ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ ተዋጊ ጄት እንዲልኩ አሜሪካ መፍቀዷን ዩክሬን በደስታ ተቀበለች።

ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ ተዋጊ ጄት እንዲልኩ አሜሪካ መፍቀዷን ዩክሬን በደስታ ተቀበለች።

ዩክራይን ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አጋሮቿ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ወደ ዩክሬን እንዲልኩ የፈቀደችበትን ውሳኔ አውድሰዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲይ ሬዝኒኮቭ እርምጃውን "በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ወዳጆቻችን (የደረሰ) ጥሩ ዜና" ብለውታል።

ዩክሬን ጄቶችን መቼ እንደምትቀበል ለጊዜው አልተገለጸም ። ጄቶቹን ለማብረር የዩክሬን አብራሪዎች አስቀድመው ሰፊ ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸውም ተነግሯል።

ተዋጊ ጄቶቹ በቅርቡ በጦርነቱን አቅጣጫ ላይ ጫና ያሳድራሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የአየር ሃይል ጄኔራል ጀምስ ሄከር አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ ዩክሬንም ሆነ ሩሲያ በአየር ላይ የበላይነቱን ሊያገኙ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ተስፋ የለም።

ሄከር ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች ብዛት በአሁኑ ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ ማንም የአየር ላይ በላይነትን የሚያረጋግጥ አይመስለኝም” ብለዋል።

በዩኤስ አየር ሃይል የአውሮፓ እና አፍሪካ አየር ኃይሎች አዛዥ የሆኑት ሄከር ዩክሬን የተቀናጀ የአየር እና ሚሳኤል መከላከያ አቅሟ የሚመናመን ከሆነ ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ጠቁመዋል ።


የኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዎፕክ ሆክስታራ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ በኤክስ አውታር ባሰፈሩት መልዕክት “F-16 ተዋጊ ጄቶች ወደ ዩክሬን ለመላክ መንገድ ከፋች የሆነውን የዋሽንግተንን ውሳኔ በደስታ እንቀበላለን” ብለዋል።