በዐማራ ክልል፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያጸድቀው ከኾነ፤ ተፈጻሚነቱ ከሳምንታት ወይም ከአንድ ወር እንዳይበልጥ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ።
የዐዋጁ ተፈጻሚነትም፣ በዐማራ ክልል ብቻ የተገደበ እንዲኾን የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ የዳኞች እና የምክር ቤት አባሎችን ልዩ መብት ጥበቃ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከግጭት ኹኔታዎች እያገገሙ ያሉት የዐማራ ክልል ከተሞች፣ ዛሬ የተሻለ መረጋጋት እንደሰፈነባቸው፣ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ባሕር ዳርንና ጎንደርን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች፤ የሰዎች፣ የተሽከርካሪዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ እንደጨመረ፣ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአንጻሩ፣ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንደሚታይ፣ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
በተያያዘ ዜና፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ በዐማራ ክልል ለተስፋፋው ግጭት፣ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጎ፣ ችግሩ በፖለቲካዊ ውይይት እና ድርድር እንዲፈታ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ ትላንት በሰጡት መግለጫ ግን፣ በዐማራ ክልል ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት፣ “ጽንፈኛ እና ዘራፊ” ያሉት ኀይል ትጥቅ እንዲፈታ፣ በመንግሥት ቅድመ ኹኔታ እንደተቀመጠ አሰታውቀዋል፡፡
ኬኔዲ አባተ በዚኹ ጉዳይ ላይ ዘገባ አሰናድቷል።
Your browser doesn’t support HTML5