በየመን ታግተው የነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ከ18 ወራት በኋላ ተለቀቁ

በባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተለቀቀው ይህ ፎቶ አካም ሶፊዮል አናም (ከግራ ሁለተኛ)፣ ሚስቱ እና ሴት ልጃቸው ከባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና ጋር ሆነው ያሳያል።


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በየመን በአልቃይዳ ክንፍ ታግተው ለ18 ወራት ታስረው የነበሩትን አምስት ሰራተኞች መለቀቃቸው ደስ እንዳሰኛቸው አስታውቀዋል።

"ዋና ጸሃፊው፣ ታጋቾቹ የደረሰባቸው መከራ ፣የቤተሰቦቻቸው እና የጓደኞቻቸው ጭንቀት በመጨረሻ በማብቃቱ በጣም እፎይታ ተሰምቷቸዋል" ሲሉ ቃል አቀባያቸው ፋርሃን ሃክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ። አክለውም ጉቴሬዝ ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ ጥሪ ማቅረባቸውን አስተውቀዋል።

አምስቱም ታጋቾች በድርጅቱ የቅድመ-ጥንቃቄ እና ደህነንት ክፍል ሰራተኛ ነበሩ። በየካቲት ወር ከደቡባዊ የአቢያን ግዛት የመስክ ተልዕኮ ወደ አደን ሲመለሱ ታግተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞቹ ከእስር እንዲፈቱ ባደረገው ድርድር ይዘት ላይ አስተያየት ባይሰጥም የኦማን መንግስት ላደረገው ድጋፍ ግን አመስግኗል። ድርጅቱ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈልን የሚከለክል ፖሊሲ አለው።

ከተጋቾች መካከል አንዱ የሆነው የባንግላዲሽ ዜግነት ያለው አክም ሱፊዩል ዕለት ወደ ዳካ ከተመለሰ በኃላ በህይወት እተርፋለሁ የሚል ሀሳብ እንዳልነበረው ተናግሯል።

“አሸባሪዎቹ በማንኛውም ጊዜ ሊገድሉኝ እንደሚችሉ አስቤ ነበር” ሲል ተናግሯል።የማሰቃየት ድርጊት ባይፈጸምበትም ብዙውን ጊዜ ዐይኖቹ ተሸፍነው ይውል እንደነበር ተናግሯል ።

የተቀሩት አራት ታጋቾች የየመን ዜጎች ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተጋቾቹ ስም ማዜን ባዋዚር፣ ባኪል አል-ማህዲ፣ መሀመድ አል-ሙላይኪ እና ካሊድ ሞክታር ሼክ እንደሚባል አስታውቋል።

ከህዳር 2021 የአውሮፓዊያኑ ዓመት ጀምሮ በሁቲ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሰነዓ ውስጥ ሁለት ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች በእስር ላይ ይገኛሉ። አንድ ዮርዳኖሳዊ የዓለም ምግብ መርሀ-ግብር ሰራተኛ በደቡብ ምዕራብ የመን ሀምሌ ወር ውስጥ በጥይት መገደሉ ይታወሳል። ዘገባው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ነው ።