የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ስትራቴጂዎቹን እየለዋወጠ የኮቪድ-19 ወረረሽኝን በተሳካ ኹኔታ ለመወጣት ቢችልም፣ የዋጋ ግሽበት ብርቱ ተግዳሮት እንደጋረጠበት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ዐዲስ አበባ ላይ ከኤኤፍፒ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ በአፍሪካ ብቸኛው አትራፊ የኾነው አየር መንገዱ፣ የዋጋ ግሽበቱ ባየለበት በአኹኑ ወቅት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማግኘት እና ተፎካካሪነቱን ይዞ ለመቆየት “ብርቱ ተግዳሮቶች” ተጋርጠውበታል፡፡
ባለፈው ሰኔ 30 ቀን ያበቃው የ2022/2023 የበጀት ዓመት፣ “እጅግ በጣም የተሳካ ዓመት ነበር” ብለዋል፣ የአየር መንገዱ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፡፡
በዚኽ የበጀት ዓመት፣ “13ነጥብ 7 ሚሊዮን መንገደኞችን አጓጉዘናል፡፡ ይህም፣ ከቀደመው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር 57 ከመቶ፣ ከኮቪድ በፊት ከነበረው ጋራ ደግሞ ሲነጻጸር የ10 ከመቶ እድገት አሳይቷል፤” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
ከዚኽ “በተጨማሪም፣ 740ሺሕ ቶን ጭነቶችን አጓጉዘናል፡፡ ከኮቪዱ በፊት ከአጓጓዝነው የጭነት መጠን እጥፍ ያህል ነው፤” ሲሉም፣ የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክለዋል፡፡
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኾነው አየር መንገድ፣ በተጠቀሰው የበጀት ጊዜ ውስጥ፣ በገቢም ደረጃ ከቀደመው ዓመት የተሻለና ብልጫ ያለው ገቢ ማስመዝገቡን፣ እ.ኤ.አ መጋቢት 2022፣ በአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የተሾሙት አቶ መስፍን ይናገራሉ፡፡
ስለዚኽ፣ በጣም ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡ የገቢ እድገት አኀዞቹም፣ ከኮቪድ ተጽእኖ ሙሉ ለሙሉ ማገገማችንን የሚያመላክቱ ናቸው፤”
“ከቀደመው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር፣ 6ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግበናል፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት ገቢ ጋራ ሲነጻጸር 20 ከመቶ ዕድገት፣ ከኮቪድ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋራ ደግሞ ሲነጻጸር የ50 ከመቶ ያህል ብልጫ አለው፤” ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
“ስለዚኽ፣ በጣም ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡ የገቢ እድገት አኀዞቹም፣ ከኮቪድ ተጽእኖ ሙሉ ለሙሉ ማገገማችንን የሚያመላክቱ ናቸው፤” ብለዋል አቶ መስፍን፡፡
አየር መንገዱ፣ የመንገደኞች ቁጥር በቀነሰበት ጊዜ፣ አንዳንድ የመንገደኞች አውሮፕላኖቹን በመቀየርም ጭምር፣ ትኩረቱን ጭነት ማጓጓዝ ላይ አድርጓል፡፡
ይህም ኾኖ፣ አቶ መስፍን እንደሚሉት፣ የወረረሽኙ ጫና፣ አሁን ድረስ ያስከተለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ በሥራ ማስኬጃ ወጪ እና በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ መልክ እየተገለጸ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ሳቢያ የተፈጠረው፣ የዓለም የሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል፣ የመለዋወጫ እጥረት አስከትሏል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የዚኽን ጉዳት ሲያስረዱ፣ “በአሁኑ ጊዜ አውሮፕላኖቻችንን እየጠገንን ለማብረር፣ ያለው የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት በጣም ጎድቶናል፤” ብለዋል፡፡ ይህም፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ችግር እንደማይኾን ተስፋቸውን ገልጸው፣ “በቀጣይ ሁለት ሦስት ዓመት ውስጥ መፍትሔ ያገኛል፤ ኢንዱስትሪውም የሚጠብቀው ይህንኑ ነው፤” ይላሉ አቶ መስፍን፡፡
መለዋወጫዎች እስኪገኙ ድረስ ለማብረር የሚቸገሩበት ጊዜ መኖሩን ያልሸሸጉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚኽም ምክንያት አንዳንዶቹ አውሮፕላኖች ለመቆም ስለሚገደዱ፣ ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተሉ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ኢንዱስትሪው፣ ኮቪድ-19 ከአስከተለው ተጽእኖ እያገገመ ሲመጣና ብዙ አውሮፕላኖች መብረር ሲጀምሩ፣ የአየር ትራንስፖርት ዋጋ የሚቀንስበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
በዚኽ የተነሣም ድርጅቱ፣ የዋጋ አወጣጥ ሥርዐቱን እንደገና መገምገም እና ተወዳዳሪ ኾኖ ለመቆየት ጠንክሮ መሥራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
አየር መንገዱ፣ በጦርነት ከታመሰችው የትግራይ ክልል የመጡ ተጓዦች ላይ “አድሎዎ ፈጽሟል” በሚል፣ የመብቶች ተሟጋች ቡድን ያቀረበውን ክሥ ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶችም እየገጠሙት እንደኾነ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
እኤአ ኅዳር 2022፣ በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ አየር መንገዱ፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል መቐለ እና ሽረ ከተሞች በረራውን ቀጥሏል። አቶ መስፍን፣ ከኤኤፍፒ የቀረቡላቸውን ከጉዳዩ ጋራ የተያያዙ ጥያቄዎች ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልኾኑ በዘገባው አመልክቷል።
አየር መንገዱ፣ በጦርነቱ ወቅት፣ ወታደር እና የጦር መሣሪያዎችን ወደ ትግራይ አጓጉዟል፤ የሚለውን ክሥ፣ ቀደም ሲል አስተባብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እኤአ ለ2050 የያዘውን ግብ ለማሳካት በሚያስችለው ዘላቂ ስትራቴጂ ላይ እየሠራ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡