ተመድ ለሶማሊያ የሚሰጠውን ርዳታ ለመቀነስ መገደዱን ገለጸ

ፎቶ ፋይል፦ የሶማሊያ ስደተኞች ሞቃዲሾ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ

በሶማሊያ ”አስጨናቂ ድንገተኛ የረሀብ አደጋ” ብለው የገለጹት አደጋ እየጨመረ አንድ ሶስተኛው ህዝብ ወደ ቀውስ ወይም ወደ ከፋ የምግብ እጥረት ደረጃ ሊደርስ ይችላል ሲሉ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሲንዲ መኬይን ትናንት ሐሙስ አስጠነቀቁ።

የተባበሩት መንግሥታት በገንዘብ እጥረት ምክንያት የምግብ ርዳታውን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እየተገደደ ነው ሲሉ ዳይሬክተሯ አክለዋል።

ሲንዲ መኬይን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት “የቅርብ ጊዜው የምግብ ዋስትና መረጃ እንደሚያሳየው፣ በከፍተኛ ጠኔ ውስጥ በህይወት ለመሰንበት በመጣጣር ላይ ያሉ የሚመስሉትን ጨምሮ፣ ከ6.6 ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን አስቸኳይ ርዳታ ይፈልጋሉ” ብለዋል፡፡

የዓለም ምግብ ድርጅት ግን በየወሩ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ለመቀነስ ተገዷል ሲሉም አክለዋል፡

ባለፈው ታህሳስ በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ለ4.7 ሚሊዮን ሰዎች ሲሰጥ የነበረው በሚያዝያ ወር ወደ 3 ሚሊዮን መውረዱን መኬይን ጠቁመዋል፡፡

አስቸኳይ የገንዘብ ድጎማ ካልተደረገ በየወሩ የምንሰጠውን ርዳታ በሚቀጥለው ሐምሌ ወደ 1.8 ሚሊዮን ዝቅ ልናደርገው እንችላለን” ሲሉም ዳይሬክተሯ አስጠንቅቀዋል፡፡

ባላፈው ወር ሶማሊያን የጎበኙት ሲንዲ መኬይን ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶማሊያውያንን ህይወት አኗኗር ለማውደም ያላቸውን አስተዋጽኖ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ የቆየውና በአስከፊነቱ የተመዘገበው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶችን ሲገድል፣ ሰብሎችንም በማበላሸት በቅርቡ በደቡብ ሶማሊያ ለደረሰው አውዳሚ የጎርፍ አደጋ መንገድ ከፍቷል ብለዋል፡፡

መኬይን ለጋሾች ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ፈጥነውሶማሊያን ከደረሰባት ከፍተኛ የረሀብ አዘቅት ለመመለስ እንዲሰሩ አሳስበዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡

ስለ ያንዥበበው አደጋ ለማሳሳሰብ ባላፈው ሚያዝያ ሶማሊያን የጎበኙት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ርዳታ ጠይቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ ግንቦት 24 በተደረገው የለጋሾች ጉባኤ፣ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመርዳት ተጠይቆ የተገኘው ገንዘብ ድጋፍ ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

ለሶስት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች፣ ለሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጠየቀ ቢሆንም የተገኘው ግን ከ1 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡