ዩኤስ-ኤአይዲ የአደጋ ምላሽ ሥርዐትን የሚያጠናክር የ12 ሚ. ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

Your browser doesn’t support HTML5

ዩኤስ-ኤአይዲ የአደጋ ምላሽ ሥርዐትን የሚያጠናክር የ12 ሚ. ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

ዩኤስ-ኤአይዲ፣ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዐትን ለማጠናከር የሚያስችል፣ የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት(ዩኤስኤአይዲ)፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው፣ የ12 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት፣ እንደ ግጭት እና ድርቅ ያሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የሚፈጥሩ ክሥተቶች በሚፈታተኗት ኢትዮጵያ፣ ለአደጋዎቹ ምላሽ ከመስጠት አንጻር የሚታዩ ውስንነቶችን እንደሚቀንስ የታመነበት ነው፡፡

ፕሮጄክቱ፣ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይና 50 ወረዳዎችን ተጠቃሚ እንደያደርግ ሲገለጽ፣ በማስጀመሪያው ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶር. ሊያ ታደሰ፣ ፕሮጀክቱ፣ በኢትዮጵያ፥ ለጤና አደጋዎች እና ወረርሽኞች የሚሰጠውን ምላሽ ለማጎልበት የሚያስችል ዐቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶር. ሊያ ታደሰ፣ በማስጀመሪያው ሥነ ሥርዐት ላይ በተገኙበት ወቅት፣ ፕሮጀክቱ፥ የጤና አደጋዎችን ለመግታት፣ ከተከሠቱም ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻል፣ ከሰው ኃይል ግንባታ ጀምሮ የሚከናወኑ ተግባራትን እንደሚደግፍ አስረድተዋል፡፡

ዩኤስ-ኤአይዲ፣ በኢትዮጵያ ከሚያደርገው የሰብአዊ ድጋፍ በተጨማሪ፣ ለጤናው ዘርፍ ብቻ፣ በዓመት ቢያንስ 200 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ የገለጹት፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ተጠባባቂ ዲሬክተር ቲሞቲ ስታይን በበኩላቸው፣ የዛሬው ፕሮጀክት፥ በሒደት፣ በኢትዮጵያ የርዳታ ጥገኝነትን ለመቀነስ እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡

‘ዩኤስ-ኤአይዲ በኢትዮጵያ፣ የጤና ዘርፉን ከመደገፍ፣ እንዲሁም የአደጋ ስጋት ምላሽ ሥርዐትንና ተቋማትን ለማጠናከር፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት፣ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደርጋል።’ ያደርጋል ያሉት ቲሞቲ “ከዚኽ ውጭ፣ ለሰብአዊ ድጋፍም፣ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እናወጣለን፡፡ ዛሬ ይፋ ያደረግነው፣ የ12 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት፣ ወደፊት የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፍላጎትን መቀነስ በሚያስችል መልኩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የአደጋ ምላሽ ዐቅምን ይፈጥራል፤ ብዬ አምናለኹ፡፡” ብለዋል።

ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ይኸው ፕሮጀክት፣ በመጀመሪያው ዓመት በሦስት ክልሎች፣ ማለትም በዐማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች፣ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 12 ወረዳዎች እንደሚተገበር ተገልጿል፡፡ በአምስት ዓመታት ቆይታውም፣ በአጠቃላይ 50 ወረዳዎችን ተጠቃሚዎች እንደሚኾኑ ታውቋል፡፡

ኤም.ኤስ.ኤች የተባለ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ጋራ በመተባበር፣ ፕሮጀክቱን እንደሚተገብሩም ተገልጿል፡፡