ሩሲያ በኪየቭ ላይ ከባድ የድሮን ጥቃት ፈጸመች

ዩክሬን ግንቦት 2015 ዓ.ም

ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪየቭ ላይ ከባድ የድሮን ጥቃት አደረሰች። ጥቃቱ፤ ሀገሪቱ ዛሬ ለሚውለው የኪየቭ የምስረታ ክብረ በዓል እየተሰናዳች ባለችበት ወቅት የተፈጸመ ነው። የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ኪልትስቾ በጥቃቱ አንድ ሰው ተገድሏል ብለዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል 50 ድሮኖች መጣሉን ያስታወቀ ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመው በኪየቭ ብቻ ይሁን በመላው ሀገሪቱ የተገለጸ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር በሩሲያ መንግስት የሚደገፉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እና የንግድ ቡድኖች ስድስት የስራ ቀናት እንዲኖሯቸው መጠየቃቸውን በዕለታዊ መግለጫው አስታውቋል። ጥያቄውን ያቀረቡት አካላትም “በጦርነት ወቅት ሀገሪቱ ለሚያሰፈልጋት ምጣኔ ሀብት ድጋፍ ለማድረግ ያለምንም ክፍያ” አንድ የስራ ቀን እንዲጨምር ጠይቀዋል ያለ ሲሆን፤ እነዚህ ቡድኖች በፊርማቸው የተደገፈ ደብዳቤ በማያያዝ ለሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸውን በትዊተር ገጹ ላይ አስታውቋል።

መግለጫው አያይዞም የሩሲያ ዋና የፕሮፓጋንዳ መሪ የሚባሉት ማርጋሪታ ሲሚንያ በጦር መሳሪያ አምራች ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ዜጎች በየቀኑ ከመደበኛው ሰዓት በተጨማሪ ሁለት ሰዓት እንዲሰሩ መጠየቃቸውን ገልጿል።