በሱዳን መጠለያቸው የወደመባቸው ኢትዮጵያውያን “ርዳታ አላገኘንም” አሉ

Your browser doesn’t support HTML5

በሱዳን መጠለያቸው የወደመባቸው ኢትዮጵያውያን “ርዳታ አላገኘንም” አሉ

በምሥራቅ ሱዳን፣ ኡምራኩባ መጠለያ ጣቢያ፣ ከኻያ ቀናት በፊት በደረሰ የእሳት አደጋ፣ መጠለያቸው የወደመባቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፥ እስከ አሁን ድረስ የመጠለያ እና የመገልገያ ቁሰቁሶች ርዳታ እንዳልተደረገላቸው፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በመሸሽ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ከትግራይ ወደ ሱዳን የተሻገሩት እነዚኹ ፍልሰተኞች፥ በሱዳኑ ውጊያ ምክንያት ቀደም ሲል የነበረው የአገልግሎት አቅርቦት መጓደሉንም ተናግረዋል፡፡ በሱዳን ካለው አለመረጋጋት ጋራ ተያይዞ፣ “ስጋት ስላለብን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሀገራችን ይመልሰን፤” ሲሉም በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም፣ “ድምፅ ይኹነን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ እስከ አሁን፣ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ይኹን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡ ስለ ስደተኞቹ ጉዳይ፣ በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቀው፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በኢሜይል በሰጠው ምላሽ፣ “ከአጋሮቼ ጋራ በመተባበር፣ የጥበቃ እና የመሠረታዊ አቅርቦቶች አገልግሎት መስጠቴን ቀጥያለኹ፤” ብሏል፡፡ ኾኖም፣ ፍልሰተኞቹ፥ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ጥያቄ እንዳላቀረቡለት፣ ኮሚሽነሩ ገልጿል፡፡

በምሥራቅ ሱዳን፣ በኡምራኩባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከሚኖሩት ስደተኞች አንዱ የኾኑት አቶ ኃይላይ ገብረ ክርስቶስ፣ ከኻያ ቀናት በፊት በተነሣ የእሳት አደጋ፣ የእርሳቸውን ጨምሮ 110 የንግድ ሱቆች እና የመኖሪያ ቤቶች እንደወደሙ ገልጸው፣ በዚኽ ምክንያት፣ 248 ስደተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን አመልክተዋል፡፡

ሌላኛዋ የቃጠሎው ተጎጂ የኾኑት ስደተኛ ወ/ሮ ሊቺያ ገብረ ሕይወት፣ ንብረታቸውን በአደጋው ከዐጡ በኋላ፣ ከእህል አቅርቦት በስተቀር ሌላ ርዳታ እንዳልደረሳቸው ይናገራሉ፡፡

በኡምራኩባ የመጠለያ ጣቢያ የማኅበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ መምህር አሉላ ወልደጅወርጊስ ደግሞ፣ በእሳት አደጋው ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁት ሰዎች፣ አስቸኳይ ርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የስደተኞቹን ኹኔታ አስመልክቶ፣ በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቀው፣ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ በኢሜይል በሰጠው ምላሽ፥ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንን በሚያስጠልሉ የገዳሪፍ የመጠለያ ጣቢያዎች፣ አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን ገልጿል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች፥ ከሱዳን የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋራ በመተባበር፣ ለስደተኞቹ የጥበቃ እና የመሠረታዊ አቅርቦቶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እነዚኹ ሠራተኞች፣ በኡምራኩባ እና በቱነድባህ መጠለያ ጣቢያዎች፣ የጤና እና የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲቀጥል ጥረት እያደረጉ ስለመኾናቸውም አስታውቀዋል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ፣ የርዳታ እህል አቅርቦት ለተወሰነ ጊዜ ቢቋረጥም፣ ከቆይታ በኋላ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለሁሉም ስደተኞች እህል ማከፋፈል መቻሉን፣ ተቋሙ በኢሜል ምላሹ አስፍሯዋል፡፡

ከፍልሰተኞቹ አንዱ የኾኑት አቶ ኃይላይ ገብረ ክርስቶስ ግን፣ እህሉ ቢገኝም፣ ብቻውን ምንም ልናደርገው አንችልም፤ ብለዋል፡፡ ከሱዳኑ ግጭት ጋራ ተያይዞ፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መጓደል እንዳለም ነው ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ፣ ከፍልሰተኞቹ ለቀረበለት፣ “ወደ አገራችን መልሰን” ጥያቄ፣ እስከ አሁን ድረስ የሰጠው አስተያየትም ይኹን ምላሽ የለም፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ቢሮ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡

ስለ ጉዳዩ የተጠየቀው የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በበኩሉ፣ ከፍልሰተኞቹ እንዲህ ዐይነት ጥያቄ እንዳልቀረበለት በኢ-ሜይል ምላሹ ጠቅሷል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ለስደተኞቹ ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ሐላፊነት አለበት ብሏል፡፡ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፅሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ እኛም ግዴታችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በምሥራቅ ሱዳን በሚገኙት፣ የቱነድባህ እና ኡምራኩባ መጠለያ ጣቢያዎች፣ ከትግራይ ተሰድደው የሔዱ ከ60ሺሕ በላይ ስደተኞች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡እነዚኽን ጨምሮ፣ ከ1ነጥብ1 ሚሊዮን በላይ

ፍልሰተኞች፣ በሱዳን ተጠልለው እንደሚገኙ፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር መረጃ ያሳያል፡፡