የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዕዳውን መክፈል የማይችልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት የብድር ጣሪያውን ከፍ ማድረግን በሚመለከት ከአንድ ስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የሀገሪቱ መሪዎች ገልጸዋል፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲው እና የዲሞክራቲክ ፓርቲው አመራሮች የብድር ጣሪያውን ከፍ ማድረግን በሚመለከት ለበርካታ ቀናት ሲነጋገሩበት ከርመዋል፡፡ እስካሁን ግን ከስምምነት ሊደርሱ አልቻሉም፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬቨን መካርቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል የወጪ ቅነሳን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ከሁሉ በፊት አንድ ነገር ለአሜሪካ ህዝብ ልናገር። ተስፋ አልቆርጥም። ዕዳችንን የመክፈል አቅማችንን አናጣም። ይሄን ችግር እንፈታዋለን፡፡ እኔም መፍትሄ እስከሚገኝ መስራቴን እቀጥላለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ እውነቱን እንናገር፡፡ ወጪያችንን ባለፈው ዓመት ከነበረው መቀነስ አለብን” በማለት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ኬቭን መካርቲ አስረድተዋል፡፡
የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒየር በበኩላቸው ሪፐብሊካኖች የጠየቁት እጅግ የበዛ የወጪ ቅነሳ እንደሆነ ገልጸው ዕዳ አለመክፈል “አማራጭ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ዕዳ ሳይከፈል ቢቀር በሀገሪቱ በጠቅላላ ከባድ ችግር ያስከትላል፡፡ የምትኖሩት ሪፐብሊካኖች በሚበዙበትም ይሁን ዲሞክራቶች እሱ ለውጥ አይኖረው፡፡ ሁሉም አካባቢ ነው የሚጎዳው” ያሉት የኋይት ሐውሷ ቃል አቀባይ “ሚሊዮኖች ስራቸውን እንደሚያጡ፡ የጡረታ ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ እንደሚመናመን እና የኢኮኖሚ ውድቀት እንደሚከሰት አመልክተዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እአአ ሰኔ አንድ ቀን ለሚጠብቁት ዕዳዎች ክፍያ የሚያውለው ገንዘብ በካዝናው ላይኖር እንደሚችል የዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ሚንስቴር ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡