የብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን የማኅበረ ቅዱሳንን ቴሌቪዥን ማገዱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች ተቃወሙ

የማኅበረ ቅዱሳን አርማ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ፣ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ “በሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በርስ ግጭት በማነሣሣት እና አለመቻቻል በመፍጠር” በሚል የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥንን ፈቃድ በጊዜያዊነት አግዷል፡፡

ባለሥልጣኑ ጊዜያዊ እግዱን ያስተላለፈው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ትላንት ከሰዓት በኋላ በአጠናቀቀው የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባው፣ በአጀንዳ ይዞ ከተነጋገረበት የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጋራ በተያያዘ፣ ዐሥር መንፈሳውያት ማኅበራት ያወጡትን መግለጫ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን “ሰበር ዜና” በሚል ማሠራጨቱን ተከትሎ ነው፡፡

የማኅበራቱ መግለጫ በጣቢያው መተላለፉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሒደውን ስብሰባ የሚያውክ እንደኾነ ማረጋገጡን የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ “ከጉዳዩ አጣዳፊነት እና ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት አንጻር” በሚል፣ የጣቢያውን ፈቃድ በጊዜያዊነት ማገዱን አስታውቋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ፣ በ“ሰበር ዜና” ያስተላለፈው መግለጫ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትገኝበት ፈተና አንጻር ወቅታዊ መረጃን ለማስተላለፍ ከተጣለበት ሓላፊነት አኳያ መታየት ያለበትና በይዘቱም፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዐት እንዲከበር፣ በአባቶች መካከል የሚታየው መከፋፈል እንዲገታ ከመጠየቅ ውጪ፣ በማንኛውም መልኩ በምእመናን መካከል ግጭት የሚፈጥር ነው ብሎ እንደማያምን በመግለጽ የጊዜያዊ እግድ ርምጃውን ተቃውሟል፡፡

ባለሥልጣኑ እግዱን ያስተላለፈበት አካሔድም፣ በዐዋጁ አንቀጽ 73 የተቀመጠውን ቅደም ተከተል ያላከበረና ሕግን የተላለፈ እንደኾነ በመግለጽ፣ ርምጃው በጣቢያው ላይ እና በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽእኖ በማገናዘብ እግዱ ተነሥቶለት አገልግሎቱን ለመቀጠል ይችል ዘንድ፣ ትላንት ለባለሥልጣኑ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የብሮድካስት አገልግሎት ተቋም ሓላፊ መስከረም ጌታቸው፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋሙ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት አለመፈጸሙን ገልጸው፣ ፕሮግራሙ የተላለፈው፥ ከዚኽ ቀደም እንደሚቀርቡት ዝግጅቶች ኹሉ፣ ለሥርጭት ከመዋሉ በፊት ይዘቱ የሚገመገምበትን የኢዲቶሪያል ሒደት አልፎ እንደኾነ ይናገራሉ።

ተቋማቸው፣ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የ24 ሰዓት ሥርጭት ሲያስተላልፍ መቆየቱን ያስታወሱት ሓላፊዋ፣ ከነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. ወዲህ፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ተመዝግቦ በሕጋዊነት እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የአሁኑ የባለሥልጣኑ ርምጃም፣ የብዙኃን መገናኛ ደንቦችንና መመሪያዎችን የጣሰ መኾኑን አመልክተዋል።

የባለሥልጣኑን የእግድ ርምጃ፣ እናት ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ)፣ እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች ተቃውመውታል።

የእናት ፓርቲ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ዳዊት ብርሃኑ፣ የባለሥልጣኑ ጊዜያዊ እገዳ፣ “መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ለመኾኑ ማሳያ ነው፤” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት አቶ ኢዩኤል ሰሎሞን፣ ፓርቲያቸው፥ መንግሥት በብዙኃን መገናኛዎች ላይ እያደረሰው ነው ብሎ ከሚያምነው ጫና ጋራ በተያያዘ መግለጫ ሲያወጣ፣ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ እንደኾነና የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የእግድ ውሳኔ እንደሚቃወመው አስታውቋል።

የማኅበረ ቅዱሳን የብሮድካስት አገልግሎት ሓላፊ መስከረም ጌታቸው፣ ተቋማቸው፣ የጊዜያዊ እግድ ውሳኔው እንዲነሣላቸው ለባለሥልጣኑ ቦርድ የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱን ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ወደ ባለሥልጣኑ ቢሮ ቢያመሩም፣ ያለቀጠሮ ልናስተናግዳችኹ አንችልም፤ የሚል ምላሽ ስለተሰጠን መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምፅ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በጊዜያዊነት የተላለፈውን እግድ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ማብራሪያ ለማግኘት፣ ከትላንት ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል። እንደተሳካልን ይዘን የምንመለስ ይኾናል።

በዚኽ ዙሪያ የተሰናዳውን ሙሉ ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ።

Your browser doesn’t support HTML5

የብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን የማኅበረ ቅዱሳንን ቴሌቪዥን ማገዱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች ተቃወሙ