የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ከትላንት በስቲያ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ፣ የዐማራ ማኅበረሰብ ተወላጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ጋራ ተገናኝተው፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና በተለይ በዐማራ ማኅበረሰብ ላይ ይፈጸማሉ በተባሉ ጥቃቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ሎሰ አንጀለስ ውስጥ የዐማራ ማኅበረሰብ ተወላጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ጋራ ተገናኝተው፣ የተወያዩት አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ይዘት እና አፈጻጸም፣ በዐማራ ክልል እና ከዐማራ ክልል ውጪ በሚኖሩ የዐማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ሌሎች የአሜሪካን ፖሊሲ የሚመለከቱ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲኾን፣ በኢትዮጵያ፣ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ያሉባቸውን ችግሮች እንደሚረዱና አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸምን ማንኛውም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተቃውማ እንደምትናገር አመልክተዋል።
"ዐዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲያችንም ኾነ፣ እኔም አጋጣሚውን በአገኘኹበት ጊዜ፣ ከዐማራ የፖለቲካ አመራሮች ጋራ ተገናኝተን ተወያይተናል። ልክ የኦሮሞ፣ የትግራይ እና ሌሎች ማኅበረሰቦችን እንደምንሰማው፣ የዐማራ ማኅበረሰብም ያለበትን ስጋት እናውቃለን። በእውነት ይህ ወቅት፣ ለኢትዮጵያውያን ፈታኝ ነው፤ ይገባኛል። ኾኖም፣ አንድ ፖሊሲ አለን። ሉዓላዊት የኾነች ኢትዮጵያን፣ የግዛት አንድነቷን በጠበቀ መልኩ የመደጋፍ እና እነዚኽን ግጭቶች እንደምን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል የመሥራት ፖሊሲ አለን፡፡”
አምባሳደር ሐመር አክለውም፣ በኢትዮጵያ የሚታዩት ወቅታዊ ችግሮች እንዲፈቱ፣ በአሜሪካ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ፣ ትልቅ ሚና እንዳለው ያስገነዘቡ ሲኾን፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ለመደገፍ ዝግጁ እንደኾነችም ጠቁመዋል።
“በጣም አስቸጋሪ ለኾኑ ጉዳዮች፣ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት እየሞከርን ነው። የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ አገሪቱ ወደፊት እንድትራመድ፣ አስፈላጊ መፍትሔዎችን ለማምጣት እና ግጭትን ለማቆም የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከሩ ባሉበት ወቅት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፏን ለመቀጠል ተዘጋጅታለች።"
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዐማራ ማኅበረሰብ አባላት፣ በዐማራ ተወላጆች ላይ ተፈጽመዋል ያሏቸውን የጋዜጠኞች፣ የመብት አቀንቃኞች እና የፖለቲከኞች እስራት፣ የኢንተርኔት መታገድ እና በታጠቁ አካላት የሚደርሱባቸውን ጥቃቶች አንሥተው ጥያቄ አቅርበዋል። ከተወያዮቹ መካከል አንዱ የኾኑት ዶር. ጌታቸው አበበ፣ ስለነበረው ውይይት የተሰማቸውን ነግረውናል።
ውይይቱን ያሰናዳው የሎስ አንጀለስ ዐማራ ማኅበረሰብ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ቤተ ልሔም ሙሉጌታ አየለ በበኩላቸው፣ የማኅበረሰቡ አባላት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፣ በዐማራ ኅብረተሰብ ላይ ይደርሳል ያሉት ጥቃት መቆም እንዳለበት ገልጸው፣ ለአምባሳደር ሐመር ያስተላለፉት መልዕክት መደመጡ ተስፋ እንደሰጣቸው አመልክተዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ሰዎች፣ በአንድነት እና በዴሞክራሲ መንገድ እንዲኖሩ ነው የምንፈልገው፤” ያሉት ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አሰፋ ድረስ በበኩላቸው፣ አምባሳደር ሐመር፣ በውይይቱ የተነሡ ሐሳቦችን በተግባር ላይ እንደሚያውሏቸው ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
"የዩናይትድ ስቴትስ ፍላጎት፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ደኅንነት ነው፤” ያሉት ሐመር፣ በሰላም፣ በትምህርት እና በጤና የመኖር ዕድል ለማግኘት እንደሚፈልጉ የሰው ልጆች ሁሉ፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ሰብአዊ ደኅንነት የአሜሪካ ትኩረት መኾኑን አስምረውበታል።
በሎስ አንጀለስ ከሚኖሩ የዐማራ ማኅበረሰብ ተወላጆች በተጨማሪ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ እና ከሶማሌ ማኅበረሰብ ጋራም እንደሚገናኙ ያስታወቁት ሐመር፣ ሁሉም ማኅበረሰቦች የየራሳቸው ስጋት እንዳለባቸው ሁሉ፣ የሚጋሯቸው የጋራ ችግሮችም በመኖራቸው፣ አብረው መሥራት እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።