የሱዳን ጦር አዛዥ፡ የአሜሪካና ሌሎች የውጭ ዜጎችን ከሱዳን ማስወጣት 'በመጪዎቹ ሰዓታት' ይጀምራል

  • ቪኦኤ ዜና

በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት የተደረሰው የተኩስ ማቆም ስምምነት ከከሸፈ በኃላ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ደጋፍ ሰጪ ሀይሉ የሚያደርጉት ግጭት እንደቀጠለ ሲሆን፣ እ.አ.አ ሚያዚያ 22፣ 2023 ዓ.ም ቅዳሜ፣ ከካርቱም ጭስ ሲወጣ ይታያል።

በሱዳን፣ ዋና የአየር ማረፊያውን ጨምሮ በመዲናዋ ካርቱም የሚካሄደው ጦርነት በመቀጠሉ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የእንግሊዝ፣ የቻይና እና የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን በወታደራዊ አይሮፕላኖች ከሀገሪቱ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት እያስተባበረ መሆኑን የሱዳን ጦር አስታውቋል።

የአሜሪካ ድምፅ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ግን የሱዳን ጦር አሜሪካውያንንም ሆነ ሌሎች የውጭ ዜጎችን ከሀገሪቱ ለማስወጣት መስማማቱን ማረጋገጥ አልቻሉም። ካርቱም ከሚገኘው ኤምባሲያቸው ጋር በቅርበት እየተገናኙ መሆናቸውንና እዛ ለሚገኙ ሰራተኞቻቸው ሀላፊነት እንዳለባቸው የገለፁት ቃል አቀባዩ "ለደህንነታቸው ሲባል ስለእንቅስቃሴያቸውም ሆነ ያሉበትን ሁኔታ ዝርዝር መነጋገር አልችልም" ብለዋል።

የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫ የጦር ሃይሉ አዛዥ ጀኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ዜጎቻቸውን እና ዲፕሎማቶቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት ከጠየቁ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር መነጋገራቸውን አስታውቋል። ሱዳን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት ስትታመስ የቆየች ሲሆን ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በሱዳን ጦር እና በተቀናቃኙ ወታደራዊ ቡድን መካከል የሚካሄደው ጦርነት የመኖሪያ አካባቢዎችን ጨምሮ፣ በዋና ከተማው ውስጥ እና በአካባቢው የሚካሄድ በመሆኑ፣ የውጭ ሀገራት በጣም አደገኛ መሆኑ የተገለፀውን ዜጎቻቸውን የማስወጣት ተግባር እስካሁን ማሳካት አልቻሉም።

ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ በመባል የሚታወቀው ልዩ ኃይል ዋናውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት፣ በካርቱም ማዕከል የሚገኘው ተቋም የከባድ ጦር መሳሪያ ድብደባ ኢላማ በመሆኑ የውጭ ዜጎችን የማስወጣቱን እቅድ አወሳስቧል። የሱዳን የአየር ክልል በመዘጋቱም፣ ማስወጣት የሚቻልበት ሁኔታ እስኪመቻች የውጭ ሀገራት ዜጎቻቸው በመጠለያዎች እንዲቆዩ አዘዋል።