ከ50 በላይ ፍልሰተኞች የሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከሞት ተረፉ

ፍልሰተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ላይ 2019

ትላንት ቅዳሜ ከሰዓት የጣሊያን የድንገተኛ ግብረ ሰናይ የነፍስ አድን መርከብ በማዕከላዊ የሜዲትራኒያን ባህር ላይ 55 ፍልሰተኞችን ሕይወት ታድጓል።

ግብረሰናይ ድርጅቱ ከፍልሰተኞቹ መካከል ሶስት ሴቶች፣ ሶስት ህጻናት እና ሶስት ወላጅ የሌላቸው ታዳጊዎች መኖራቸውን አስታውቋል። ፍልሰተኞቹ በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ 10 ሜትር እርዝመት ባላት እና አንደኛው ሞተሯ በተበላሸ አነስተኛ ጀልባ ከሊቢያ ጠረፍ ተነስተው ሲሄዱ መታየታቸውን የነፍስ አድን ቡድን ተልዕኮ ዋና ሃላፊ ኢማኑኤል ናኒኒ አስታውቀዋል።

ግብረሰናይ ተቋሙ ከሶስት ቀናት በኋላ ፍልሰተኞቹን ሰላማዊ በሆነው በሰሜናዊ ጣሊያን ማሪና ዲ ካራራ ለማሳረፍ ሃሳብ መኖሩን አስታውቋል። ፍልሰተኞቹ ከአይቮሪኮስት፣ ግብጽ፣ ኤርትራ፣ ናይጄሪያ፣ ፍልስጤም፣ ሱዳን እና ሶማሊያ የመጡ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ እ.ኤ.አ. የ2023 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባህር ከባለፉት 6 ዓመታት ውስጥ በላቀ፤ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጀልባዎች ለሚያቋርጡ ፍልሰተኞች ገዳይ የሆነው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ነው ሲል አስታውቋል።

ኤጀንሲው አክሎም ይህም የሀገራት የነፍስ አድን ሂደት በመዘግየቱን ምክንያት የተከሰተ ነው ሲል ጠቅሷል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በጥር ፣ በየካቲት እና መጋቢት ወራት በሰሜናዊ አፍሪካ እና በአውሮፓ ደቡባዊ የባህር ዳርቻዎች መካከል ባለው አደገኛ የባህር መስመር 441 ስደተኞች መሞታቸውን ዘግቧል ። እ.ኤ.አ. በ 2017 በተመሳሳይ ጊዜ 742 የታወቁ ሰዎች ሞት ተመዝግቧል ፣ በ 2015 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ደግሞ 446 መሞታቸው ይታወሳል።