የአይሻ ከተማ ለተቃውሞ መዘጋቱን ተከትሎ ኹለት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

የአይሻ ከተማ ለተቃውሞ መዘጋቱን ተከትሎ ኹለት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

በአፋር ክልል፣ ያለአግባብ ተፈናቅለዋል ያሏቸው የሶማሌ ተወላጆች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በሚል አገር አቋራጭ መንገድ ዘግተው በነበሩ የአይሻ ከተማ ነዋሪዎች ላይ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ወሰዱት በተባለ የኃይል ርምጃ፣ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። በጉዳዩ ላይ፣ ከመከላከያ ሰራዊትም ኾነ ከፌዴራል መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ከደቡብ ጅቡቲ 46 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሶማሌ ክልል አይሻ ከተማ ነዋሪዎች፣ ከአፋር ክልል ያለአግባብ ተፈናቅለዋል ያሏቸው የሶማሌ ተወላጆች፣ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በመጠየቃቸው፣ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚወስደውን ዋናውን አገር አቋራጭ መንገድ ለኹለት ቀናት ዘግተውት እንደነበር፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት፣ ብዙ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ የሲቲ ዞን አደጋ መከላከል አስታውቋል፡፡ ኹለቱ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው ሦስት ቀበሌዎች እና በአጎራባች አካባቢዎች፣ የአፋር ታጣቂዎች ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት የተፈናቀሉ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የሶማሌ ብሔር ተወላጆች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በመጠየቅ፣ እሑድ መጋቢት 17 እና ሰኞ መጋቢት 18 ቀን መንገድ መዝጋታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ባለፈው እሑድ አመሻሽ ላይ፣ የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ ገብቶ፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋራ ውይይት ማድረጉን፣ ኾኖም በውይይቱ ከስምምነት ባለመደረሱ ግጭት መፈጠሩንና ሰዎች መገደላቸውን በስልክ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪ ሮብሌ መሐመድ ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተዋል። ጥቃቱ የደረሰው፣ የጸጥታ ስጋት ባልነበሩ ሰዎች ላይ ነው፤ በማለት ወቀሳ ያሰሙት አቶ ሮብሌ፣ በዕድሜ የገፉ አክስታቸው የጥቃቱ ሰለባ መኾናቸውን፣ በአስረጅነት ጠቅሰዋል።

የአይሻ አካባቢ ተወላጅ እና የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ዓሊ ሰሚሬም፣ ስለዚሁ ጉዳይ ሲያስረዱ፣ ሰኞ ረፋድ ላይ የመከላከያ አመራሮች ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋራ ከተወያዩ በኋላ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አገር አቋራጭ መንገዱ፣ ሰኞ ከቀትር በኋላ ጀምሮ ክፍት ቢኾንም፣ የባቡር ሐዲዱ ግን በተቆጡ የከተማዋ ወጣቶች በመነቃቀሉ አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን አቶ ዓሊ ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል።በአሁኑ ሰዓት፣ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በአይሻ ከተማ እንደሚገኙ የገለጹልን አቶ ዓሊ፣ በከተማዋም ስጋት ማንዣበቡን አመልክተዋል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን፣ ወደ ወረዳዋ ሊቀ መንበር አቶ አብዲ ፉሬ እና ሌሎችም የወረዳዋ አመራሮች ስልክ ላይ፣ ከሰኞ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተደጋጋሚ ብንሞክርም፣ የብዙዎቹ በመዘጋቱ አንዳንዶቹም ባለመመለሳቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። የሲቲ ዞን ሊቀ መንበር አቶ መሐመድ ረቤ እና ሌሎች የሲቲ ዞን አመራሮችም፣ የእጅ ስልካቸው በመዘጋቱ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡የመከላከያ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነንም፣ በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በአሁኑ ሰዓት በሦስት የተለያዩ ዙሮች፣ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት የተፈናቀሉ ከ300ሺሕ በላይ ዜጎች፣ በሲቲ ዞን እንደሚገኙ የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ቢሮ ሓላፊ አቶ ሐሰን ረቤ ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ሐሰን ረቤ ገለጻ፣ ከ49ሺሕ200 በላይ አባዎራዎች ተፈናቅለዋል። ለተፈናቃዮቹ ልዩ ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ቢኾንም፣ ከችግሩ ስፋት አንጻር ግን በቂ እንዳልኾነ አቶ ሐሰን ገልጸዋል። በተለይም የአልሚ ምግብ እጥረት መኖሩን አጽንዖት ሰጥተውበታል።

ከሦስቱ አወዛጋቢ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፣ አስቀድሞ የከተማ ነዋሪዎች በመኾናቸው፣ ምንም ዐይነት መሠረተ ልማት በሌለበት ቦታ፣ ያለበቂ መጠለያ መስፈራቸው ለልዩ ልዩ ችግር እንደዳረጋቸው የቢሮው ሓላፊ አስገንዝበዋል።

በጉዳዩ ላይ፣ የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ አቶ አሕመድ ካሎይታ፣ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

የአፋር እና ሶማሌ ክልል በሚወዛገቡባቸው በሦስቱ ቀበሌዎች ሳቢያ፣ ተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ ገብተዋል፤ ተደጋጋሚ የሰላም ጉባኤዎችንም አካሒደዋል። ኾኖም እስከ አሁን ድረስ፣ ደም መፋሰሱ እያሠለሰ እንደቀጠለ ነው።