የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት በቅርቡ ያወጣው የሰብአዊ መብት ሪፖርት፣ ከጣምራ ቡድኑ ሪፖርት ጋራ በአመዛኙ ተመሳሳይ እንደ ኾነ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ስለተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ማይክ ሐመር ጋራ መወያየታቸውንም ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አያይዘውም፣ ለተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ማብራሪያ መስጠታቸውን ጠቅሰው፣ ምክር ቤቱ ሙሉ ድጋፉን እንደ ቸረ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ማይክ ሐመር ጋራ፣ በተጠያቂነት እና የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት ዙሪያ መወያየታቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ከልዩ ልኡኩ ጋራ በነበራቸው ቆይታ፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ፣ ኢሰመኮ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጣምራ ያካሔዱትን ጥናት ተከትሎ፣ በአቀረቡት ምክረ ሐሳብ ላይ በመመሥረት እየተካሔደ ስለአለው የሽግግር ፍትሕ ሒደት መወያየታቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
“የጣምራ ቡድኑ በጥናት ሪፖርቱ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች፣ በተለይም የሽግግር ፍትህ አስተዳደር ጽንሰሃሳብ እንዴት እየተፈጸመ እንደሆነ ብዙዎቹ ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ አጋሮች ከእኛ ጋር ይመካከራሉ፤ ሀሳብ ይለዋወጣሉ” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የዚህ አካል እንደሆነ በገለጹትና ከማይክ ሃመር ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም በዋናነት “በሽግግር ጽንሰሃሳብ አተገባበር ላይ ነው ሃሳብ የተለዋወጥነው” ብለዋል፡፡
የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ውጤታማ እንዲኾን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንደምታደርግ ልዩ ልኡኩ ማይክ ሐመር ማስታወቃቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ አማራጭ ፖሊሲዎች ላይ ውይይት በተጀመረበት ወቅት፣ ተጠያቂነትን ያካተተ የሽግግር ፍትሕ ሒደት መከናወን እንደዳለበት ከልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋራ ባደረገው ውይይት ያሰባሰበው ግብዓት እንደሚያመለክት፣ ኢሰመኮ ቀደም ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከሚኒስትሩ ጋራ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሩ፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከዋና ኮሚሽነር ዳንኤል እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋራ ከአደረጉት ውይይት በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ “ኢትዮጵያውያን ኹሉን አቀፍ የኾነ የሽግግር ፍትሕ ሒደት ለማከናወን በገቡት ቃል መሠረት እንዲያስፈጽሙ እናሳስባለን፤” ያሉት ብሊንከን፣ “ይህም እርቅንና ተጠያቂነትን የሚያካትት ሊኾን ይገባል፤” በማለት ማሳሰባቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 11 ቀን በአወጣው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት ደግሞ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለኹለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት የተሳተፉ ኹሉም ኀይሎች፣ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፤ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን፣ ሪፖርቱን ይፋ በአደረጉበት ወቅት፣ “የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የኤርትራ መከላከያ እና የአማራ ኀይሎች፥ ግድያን፣ አስገድዶ መድፈርንና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶችን፣ ከቤት ንብረት ማፈናቀልን ጨምሮ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ፈጽመዋል፤” ያሉ ሲኾን፣ ህወሓትን ግን ለእነዚህ ወንጀሎች ተጠያቂ አላደረጉም፡፡
“ኹሉም ወገኖች ለፈጸሙት ግፍ በይፋ እውቅና መስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ ርምጃ ነው” ያሉት ብሊንከን፣ “በአዛዥነት ቦታ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ለተፈጸሙት የጭካኔ ተግባራት ተጠያቂ የኾኑ አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው፤” በማለት አሳስበዋል፡፡ ኹሉን አቀፍ የሽግግር የፍትሕ ሒደት እንዲተገበርም እንዲሁ፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው፣ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል፣ “በአሜሪካ መንግስት የቀረበው ሪፖርት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት በጣምራ ባደረግነው ምርመራ ከደረስንበት ድምዳሜ ብዙ የተለየ ወይም ብዙ የራቀ አይደለም፤ አብዛኛው ተመሳሳይ ነው” ብለዋል፡፡ ዝርዝር ተጠያቂነትን በሚመለከት ግን፣ የትኛው አካል ምን አይነት ወንጀል ተፈጸመ የሚለውን ለመለየት የሚደረገው ምርመራ የወንጀል ምርመራ ስራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ “ከዚያ ውጭ የጣምራ ቡድኑ ድምዳሜና የአሜሪካ መንግስት የደረሰበት ድምዳሜ ብዙ የሚራራቅ አይደለም” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የሰጠችው መግለጫ፣ “ወገናዊ እና ተንኳሽ ነው፤” ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ መግለጫውን እንደማይቀበለው መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ሒደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረው እንደኾን አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ “ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ስራ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርመራና ምምረሃሳብ የሚመራ እንጂ በአንድ ሀገር ሪፖርት ላይ የሚመሰረት አይደለም ለማለት ይመስለኛል እንጂ የተፈጸመውን ድርጊት ሙሉ በሙሉ የመካድ ነው ብዬ አላምንም” ብለዋል፡፡ ለዚህም፣ መንግስት በጣምራ ቡድኑ የቀረበለትን ምክረሃሳብ ከመተግበር አንጻር እየወሰዳቸው ነው ያሏቸውን እርምጃዎች በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
በጄኔቫ እየተካሔደ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 52ኛ ጉባኤ ላይ፣ ከትላንት በስቲያ ተገኝተው በኢትዮጵያ ለተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ምክረሃሳብ ማቅረባቸውንና ይህም በምክርቤቱ አባሎች “ሙሉ ድጋፍ” ማግኘቱንም ነው ዋና ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ የገለጹት፡፡
ባለፈው መስከረም፣ የሥራ ጊዜው በአንድ ዓመት የተራዘመለት እና በተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ፣ የሥራ ጊዜው ከተራዘመ በኋላ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ፣ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ሲያቀርብ፣ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ እና የስምምነቱ አንዳንድ ነጥቦች እየተተገበሩ መኾናቸውን በአዎንታዊነት ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል፣ የስምምነቱ አካል የኾኑትን፣ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊነት ለመደገፍ፣ ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ምርመራ በአለበት ኾኖ በርቀት መቀጠሉን ገልጿል፡፡ ጦርነቱ ወደተካሔደባቸው አካባቢዎች አቅንቶ ምርመራ ለማድረግ፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ እስከ አሁን ተቀባይነት አለማግኘቱንም ኮሚሽነሮቹ አስታውቀዋል፡፡
“ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ ነው” በማለት አቤቱታ ያቀረበው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኮሚሽኑ እየተከናወኑ ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ተግባራት እንዲቆሙ የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ ማዘጋጀቱን፣ በቅርቡ በዐዲስ አበባ በተካሔደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ መግለጹ እና ለዚኽም ድጋፍ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡
ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡