ትራምፕ ማክሰኞ እንደሚታሰሩ አስታወቁ

  • ቪኦኤ ዜና

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከማንሃታን አውራጃ አቃቤ ህግ ቢሮ ሾልኮ የደረሳቸው መሆኑን በገለፁት እርምጃ መሰረት ማክሰኞ እለት እንደሚታሰሩ በማህበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ዛሬ ለተከታታዮቻቸው አስታውቀዋል።

ትራምፕ የራሳቸው ማህበራዊ ሚዲያ በሆነው 'ትሩዝ ሶሻል' ባስተላለፉት መልዕክት ለደጋፊዎቻቸው "ተቃውሞ አሰሙ፣ ሀገራችንን መልሰን እንውሰድ" ሲሉ ጥሪ አቀርበዋል። ለምን እንደሚታሰሩ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።


በኒውዮርክ ከተማ የሚገኙ ባለስልጣናት ግለሰቦች መረጃ እንዳያወጡ ዝም ለማሰኘት ገንዘብ በመክፈል ወንጀል በትራምፕ ላይ ክስ መመስረት የሚቻልበትን ሁኔታ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ከአንዲት የወሲብ ፊልሞች ላይ ከምትተውን ሴት ጋር ነበራቸው የተባለው ግንኙነት ይፋ እንዳይወጣ ዝም ለማሰነኘት ገንዘብ ከፍለዋል ተብሏል።

በትራምፕ ላይ የቀረበ ምንም አይነት የወንጀል ክስ ስለመኖሩ ከባለስልጣናት የተረጋገጠ ነገር የለም። ሆኖም የኒውዮርክ ከተማ የህግ አስከባሪ ተቋማት ትራምፕ ክስ ሊመሰረትባቸው ከቻለ ሊደረጉ ስለሚገቡ የፀጥታ ዝግጅቶች ላለፉት ጥቂት ቀናት ሲወያዩ መቆየታቸውን አንዳንድ የሚዲያ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ትራምፕ የሚታሰሩ ከሆነ ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው እ.አ.አ በጥር 6፣ 2021 ዓ.ም በአሜሪካ ምክርቤት ህንፃ ላይ ጥቃት ከመድረሱ በፊት በኢንተርኔት ላይ ያደረጉትን ቀስቃሽ ንግግር ያስተጋባ መሆኑ ተገልጿል።

ትራምፕ በወንጀል ከተከሰሱ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሲታሰሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።