በብሩንዲ አንድ የአራት አመት ህጻን እና ከልጁ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሁለት ህፃናት ላይ የፖሊዮ በሽታ ከተገኘ በኃላ፣ የሀገሪቱ መንግስት ብሄራዊ የህዝብ ጤና አስቸኳይ አዋጅ አውጇል።
የፖሊዮ ወረርሽኝ በብሩንዲ ሲከሰት ከ30 አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከህፃናቱ በተጨማሪ የጤና ባለስልጣናት አምስት የፖሊዮ ናሙናዎችን በቆሻሻ ውሃ ላይ በማግኘታቸው ሁለተኛው አይነት የፖሊዮ ቫይረስ እየተዘዋወረ መሆኑን አረጋግጠዋል። በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ የሆነው ይህ በሽታ በተበከለ ውሃ እና ምግብ ወይም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ይተላለፋል።
የሀገሪቱ መንግስት አዲስ ከተወለዱ ህፃናት ጀምሮ እስከ ሰባት አመት ላሉ ህፃናት የሚሰጥ የክትባት ዘመቻ እያዘጋጀ ሲሆን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ መሰጠት እንደሚጀምር ተገልጿል።