ተመድ – ከኢራን ጋር በሚደረገው ንግግር ትልቅ ተስፋ አለ

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተመልካች ተቋም ጋዜጣዊ መግለጫ በቴህራን

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተመልካች ተቋም ኃላፊ ከኢራን ጋር የሳይንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከኢራን ጋር ንግግር መኖሩንና ሂደቱም “ትልቅ ተስፋ ማሳደሩን” ዛሬ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡፡

የተቋሙ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ በቴህራን የሚያደርጉት ስብሰባ የተጀመረው ትናንት መሆኑ ሲገለጽ፣ ዲፕሎማቶች የስብሰባው ዓላማ ከዓለም አቀፉ የኒውክለ መርማሪ ተቋም ጋር ኢራን እንድትተባበር ግፊት ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ግሮሲ በቴህራን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ በግልጽ እንደሚታየው ኢራን እና ተቋሙ በጋራ እየሰራንባቸው ያሉት ጉዳዮች ወደፊት እንዲቀጥሉ፣ በኢራን ስላለው የኒውክለር ፕሮግራም ግልጽ ለማድረግና ማረጋገጫዎችን ለመስጠት ትልቅ ተስፋ አለ” ብለዋል፡፡

ከኢራን የአውቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ኃላፊ መሀመድ እስላሚ ጎን ቆመው መግለጫ የሰጡት ግሮሲ “ሁለተኛው ጉዳይ፣ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነው በሳይንስና ቴክኒክ ዘርፍ ከኢራን ጋር ያለንና ወደፊትም የሚቀጥለው ትብብርን በሚመለከት ነው” ብለዋል፡፡

ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር “በሥራ፣ በታማኝነትና፣ በትብብር” መንፈስ እየተካሄደ መሆኑንም የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ተናግረዋል፡፡

የኃላፊው ጉብኘት የመጣው ኢራን በፎርዶው የኒውክለር ማበልጸጊያ ተቋም የኒውክለር ኃይል ለማመንጨት የሚያስችላትን የዩራኒየም ንጥረ ነገር መጠን ወደ 83.7 ከመቶ ባደረሰችበትና የኒውክለር ጦር መሳሪያ ለመስራት ወደ 90 ከመቶ እየተጠጋችበት ባለችበት ወቅት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የኒውክለር ተመልካች ቡድን ሪፖርትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የአቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ኃላፊ መሀመድ እስላሚ ግን የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የዩራኔየም መጠንኗ ወደ 60 ከመቶ ማድረሷን ዛሬ ቅዳሜ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡