በተመድ የሚደረገውን ምርመራ ለማስቆም ኢትዮጵያ ድጋፍ እያሰባሰበች ነው

ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ወቅት የጅምላ ዕልቂት፣ አስገድዶ መድፈርና ካለፍርድ መታሰር የመሰሉ በደሎች ተፈጽመዋል በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እያደረገ ያለውን ምርመራ ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ነው ሲል 5 ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ይህም የአፍሪካ አገራትንና የምዕራቡን ዓለም ሊከፋፍል ይችላል ሲል ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችና በህወሓት ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመት የተደረገው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት በተደረሰ የሰላም ሥምምነት ቢያበቃም፣ ለደረሰው ሰቆቃና በደል አንዱ ሌላውን ተጠያቂ አድርጓል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

መሠረቱን በጀኒቫ ያደረገው የተመድ የሰብዊ መብቶች ም/ቤት የሚያደርጋቸውን ምርመራዎች ከዚህ በፊት አቋርጦ ባያውቅም፣ ኢትዮጵያ ም/ቤቱ እያካሄደ ያለውን ምርመራ እንዲያቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በማሠራጨት ላይ ነች። ሃሳቡ የምርመራ ውጤቱ እንዳይታተምና በምክር ቤቱም ክርክር እንዳይደረግበት የሚጠይቅ ነው ብሏል ሮይተርስ በተለይ ባወጣው ሪፖርት።

ም/ቤቱ የመደባቸው ሦስት ገለልተኛ መርማሪዎች በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች ሁሉ የጦር ወንጀልና ሌሎች ሰቆቃዎችን ለመፈጸማቸው “አሳማኝ ሁኔታዎች አሉ” በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ሥራቸውን ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ሃሳብ 47 ዓባላት ላሉት የሰብዓዊ ም/ቤት ገና በይፋ አልቀረበም። ም/ቤቱ እስከ መጋቢት 26 የሚቆየውን ዓመታዊ ስብሰባ ትናንት ሰኞ የጀመረ ሲሆን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሁለት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ግፊቷን እንድታቆም ለማግባባት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

“መጥፎ ምሳሌ የሚሆን ነው” ብለዋል አንድ ምዕራባዊ ዲፕሎማት።

በአፍሪካውያን ዘንድ ግን ለምርመራው የሚሰጠው ድጋፍ እየቀነሰ ነው ተብሏል። ባለፈው ጥቅምት የመርማሪ ቡድኑ የሥራ ግዜ መራዘምን ሁሉም የአፍሪካ አገራት ተቃውመውታል። ለተጨማሪ ዓመት ምርመራው የተራዘመው በጠባብ የድምጽ ብልጫ ነበር።

ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ ላይ ድምጽ የሚሰጥ ከሆነ፣ መርማሪ ቡድኑን ያቋቋመው የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ምዕራብዊያን አገሮችን ከአፍሪካውያኑ ጋር ሊያፋጥጥ ይችላል። በተከፋፈለው የሰብዓዊ ም/ቤት ውስጥ ምዕራባዊያኑ በቻይናና በሩሲያ ላይ ለሚያራምዱት አቋም የአፍሪካውያኑን እገዛ ይሻሉ።

“ትልቅ ትግል ነው የሚሆነው” ብለዋል የምርመራውን መቋረጥ የማይደግፉ አንድ ዲፕሎማት።

በም/ቤቱ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሚሼል ቴይለር ኢትዮጵያ ምርመራው እንዲቆም ሃሳብ አላት የሚለውን አረጋግጠዋል። “ይህ የሚፈጥረውን መጥፎ ምሣሌ እንቃወማለን። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለሚታየው ሂደትና መልካም ለውጥም የሚበጅ ነው ብለን አናስብም” ብለዋል አምባሳደሯ።