እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ጥቃት የአየር ጥቃት አደረሰች

  • ቪኦኤ ዜና

እ.አ.አ የካቲት 23፣ 2023 ጠዋት እስራኤል በፍልስጤም ግዛት ላይ የአየር ጥቃት ከአካሄደች በኃላ በጋዛ ከተማ ከሚገኙ ሕንፃዎች በላይ ጭስ ሲወጣ ይታያል።

የእስራዔል የጦር ኃይል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ማካሄዱን አስታወቀ፡፡ የአየር ጥቃቱ የተካሄደው በሰዓታት ቀደም ብሎ ወደእስራኤል ግዛት ለተተኮሱት ሮኬቶች አጸፋ ለመመለስ መሆኑን የጦር ኃይሉ አስታውቋል፡፡

የአየር ጥቃቱ ያነጣጠረው ጋዛ ውስጥ በሚገኙ አንድ የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና ወታደራዊ ግቢ ላይ መሆኑን የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች አመልክቷል፡፡

ከጋዛ ከተተኮሱት ስድስት ሮኬቶች ውስጥ ደቡባዊ እስራኤል ውስጥ ከወደቀው ከአንዱ በስተቀር አምስቱን መምታታቸውን የእስራኤል ኃይሎች ገልጸዋል፡፡

ድንበር ተሻጋሪው የሮኬት ጥቃት የተካሄደው ትናንት ረቡዕ እስራኤል በዌስት ባንክ ያካሄደችውን እና አስራ አንድ ሰዎች የተገደሉበትን ወረራ ተከትሎ መሆኑን ዜናው አውስቷል፡፡

ወረራውን ያካሄደችው ናብሉስ ከተማ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችን ለመያዝ መሆኑን የገለጸችው እስራኤል የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ኃይሎቻችን ላይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ ነው ብላለች፡፡

የፍልስጥኤም የጤና ባለስልጣናት በጥቃቱ ከአንድ መቶ በላይ ፍልስጣኤማውያን እንደቆሰሉ ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ትናንት ረቡዕ በድርጅቱ ስብስባ ላይ ባደረጉት ንግግር የግጭቱ ሁኔታ በዐመታት ውስጥ ከታየው ሁሉ የከፋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዋሽንግተን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ሁለቱ ወገኖች ውጥረቶቹን የሚያባብስ ዕርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡