አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን 'በሰው ልጆች ላይ ወንጀል' መፈጸሟን አስታወቀች

  • ቪኦኤ ዜና
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስ በሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉት - የካቲት 18፣ 2012

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስ በሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉት - የካቲት 18፣ 2012

ሩሲያ አንድ አመት ሊሞላው በተቃረበው የዩክሬን ወረራ "በሰው ልጆች ላይ ወንጀል" ፈፅማለች ሲል የባይደን አስተዳደር በይፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስ ዛሬ አስታወቁ።

የቀድሞ አቃቤ ህግ የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ኻሪስ በሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ላይ ዛሬ ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የምታደርገውን በተመለከተ ማስረጃዎችን መርምረናል፣ የህግ ደረጃዎችን እናውቃለን፣ እናም እነዚህ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም" ብለዋል። ኻሪስ አክለው "እነዚህን ወንጀሎች የፈፀሙ እና በነዚህ ወንጀሎች ተባባሪ የሆኑት አለቆቻቸው ተጠያቂ ይሆናሉ" ብልዋል።


በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራው የህግ ትንታኔ የደረሰበት ድምዳሜ አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ምንም አይነት የሚያስከትለው ተፅእኖ ባይኖርም፣ ዋሽንግተን የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የበለጠ ለማግለል እና የመንግስታቸውን አባላት በዓለም አቀፍ ፍርድቤቶች እና እገዳዎች ተጠያቂ ለማድረግ ይረዳል ብላ ተስፋ ታደርጋለች።

የዩክሬንን ጉዳይ የሚከታተለው እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው አጣሪ ኮሚሽን ግን እስካሁን የተፅሟል ያለው የጦር ወንጀል 'በሰው ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል' ለመሆኑ እስካሁን ድምዳሜ ላይ አልደረሰም።