በሱዳን ለሚገኙ ፍልስተኞች 500 ሚሊዮን ዶላር ተጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ከ41 ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ አገሮች ጋር በመሆን እኤአ በ2023 በሱዳን ለሚገኙ 900ሺ ስደተኞች የሚያስፈለገውን የ500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተማጽኖ ከትናንት ማክሰኞ ጥር 23/2015 ጀምሮ ይፋ ማድረጉን የመንግሥታቱ ድርጅት ረዳት ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫቸው እርዳታው የህይወት አድን ድጋፍን ለማድረስ ያለመና፣ እንዲሁም በሰብአዊና የልማት ተዋናዮች መካከል መሰረታዊና የተቀናጁ ግንኙነቶችን እንዲኖሩ ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀቅ አክለውም፣ ሱዳን በአፍሪካ ሁለተኛዋ የፖለቲካ ጥገኞችን ተቀባይ አገር ስትሆን ከደቡብ ሱዳን ኤርትራ ኢትዮጵያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ቻድ ሶሪያ የመን እና ከሌሎች አገሮች የመጡ ወደ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስተኞችን ታስተናግዳለች” ብለዋል፡፡