አል ሻባብ በሶማሊያ የጦር ሠፈር ላይ ጥቃት አደረሰ

  • ቪኦኤ ዜና

የሶማሊያው ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ ዛሬ በአንድ የሀገሪቱ የጦር ሠፈር ላይ ጥቃት አድርሷል።

ጥቃቱ የደረሰው የሶማሊያ መንግሥት በቡድኑ ተይዛ የነበረች ቁልፍ የጠረፍ ከተማ በማስለቀቅ "ታሪካዊ ድል ተቀዳጅተናል" ባለ ማግሥት መሆኑ ነው።

ከዋና ከተማዋ ከሞቃዲሾ በስተሰሜን ባለችው ሃዋድሌ ከተማ በዛሬው ዕለት ታጣቂው ቡድን ባደረሰው ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ የተለያየ አሃዝ እየወጣ ነው።

የጦር ሠራዊቱ አዛዥ ኦዶዋ ዩሱፍ በመንግሥቱ የራዲዮ ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በጥቃቱ አንድ ከፍተኛ መኮንን ጨምሮ አምስት ወታደሮች እንደተገደሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የደረሰባት ከተማ አቅራቢያ የሚንቀሳቀስ አንድ ሚሊሽያ አዛዥ ደግሞ የተገደሉት 11 ወታደሮች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አል ሻባብ ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።