በመቶ የሚቆጠሩ ግራ ዘመምና ለዘብተኛ ማኅበራዊ አንቂዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታንያሁን አዲስ መንግስት ምሥረታ ሥነ-ሥርዓት በመቃወም በአገሪቱ ፓርላማ ደጃፍ ላይ ሰልፍ አድርገዋል።
የቀኝ ዘመሙ የእስራኤል መንግስት በዌስት ባንክ የአይሁድ ሠፈራዎችን ለማስፋፋት በያዘው ውጥንና በሌሎቹም ፖሊሲዎቹ ምክንያት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ትችት ገጥሞታል። ሁኔታው ግን ቤንጃሚን ናታንያሁን ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነት ተመልሰው ሥልጣናቻውን እንዲያጠናክሩ ረድቷል ተብሏል።
ባለፈው ወር በተደረገው ምርጫ ሃይማኖታዊና አክራሪ የሆኑ ፓርቲዎች ስብስብ አብላጫ ወንበር መያዙን ተከትሎ፣ በሙስና ቅሌት በክስ ላይ ያሉት የ73 ዓመቱ ናታንያሁ የሲቪል መብቶችና የዲፕሎማሲን የወደፊት ዕጣ በተመለከተ የተፈጠረውን ስጋት ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውለዋል።
ጺዎናዊነትንና የአይሁድ የበላይነትን የሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ከናታንያሁ አጋሮች ጥቂጦቹ ሲሆኑ፣ የፍልስጤምን ሉአላዊ አገር መሆን የሚቃወሙና በዌስት ባንክ ያሉ እዳጣን አረቦችን መብትና የተመሳሳይ ጾታን ግኑኘትን የሚቃወሙ ናቸው።
መቻቻልንና ሰላምን ለማስፈን እንደሚሠሩ ናታንያሁ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ተቃውሞ ሠልፍ አድራጊዎቹ ግን አዲሱ መንግስታቸው ዲሞክራሲ ላይ የተጋረጠ አደጋ እንደሁነ ይመለከቱታል።