ድምፃዊ ገ/እግዚአብሄር ገ/ፃዲቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

  • ቪኦኤ ዜና

የትግርኛ ዘፋኝ ገ/እግዚአብሄር ገ/ፃዲቅ

ታዋቂው የትግርኛ ዘፋኝ ገ/እግዚአብሄር ገ/ፃዲቅ በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ድምፃዊ ገ/እግዚአብሄር ገ/ፃዲቅ በትናንትናው ዕለት ድንገት ማረፉን የአርቲስቱ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት አቶ ተመስገን ደመወዝ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል፡፡

የ66 ዓመቱ ድምፃዊ ረቡዕ ዕለት ወደ ሆስፒታል እንደሄደና በነገታው ትናንት ሐሙስ ምሽት ማረፉን አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

ድምፃዊ ገ/እግዚአብሄር በ1949 ዓ.ም በዓዲግራት ከተማ ነበር የተወለደው፡፡ ከሙዚቃ ጋር በልጅነቱ የተዋወቀው ገ/እግዚአብሄር በ 1973 ዓ.ም ከዓዲግራት ወደ አስመራ በመሔድ የሙዚቃ ሙያውን ማሳደግ ችሏል፡፡ በአስመራ ከተማ ያሬድ ሙዚቃ ቤት የሚባል መደብር በመክፈት የበርካታ ድምፃውያንን ስራ ያሳትም እንደነበረም የሙያ ባልደረባው አርቲስት ደበሳይ ዘገዬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሯል፡፡

ድምፃዊና የክራር ተጫዋች የነበረው አርቲስት ገ/እግዚአብሄር በህይወት ዘመኑ አስር አልበሞችን ያሳተመ ሲሆን የስቱድዮ ስራቸው የተጠናቀቁ ሁለት አልበሞችን ለመልቀቅ ሲዘጋጅ እንደነበር ጓደኛው አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ገ/እግዚአብሄር ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የመጨረሻ ካሴቱን የለቀቀው በ 1992 ዓ.ም ነበር፡፡

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አርቲስት ገ/እግዚአብሄር፣ የቀብር ስነስርዓቱ ዛሬ ከሰዓት በአዲስ አበባ አስኮ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡