“ለዩክሬን የሚሠጥ ገንዘብ ችሮታ አይደለም” ዜሌንስኪ ለአሜሪካ ኮንግረስ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዜለንስኪ ለሁለቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምክርቤቶች የጋራ ጉባኤ ንግግር ካደረጉ በኃላ የአሜሪካ ምክርቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በስጦታ ያበረከቱላቸውን የአሜሪካ ባንድራ ይዘው ታህሳስ 21, 2022.

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ትናንት በአሜሪካ ኮንግረስ ባደረጉት ንግግር አገራቸውን መርዳት ችሮታ ሳይሆን የዓለም ደህንነትንና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚውል መዋዕለ-ነዋይ ነው ብለዋል።

ትናንት በድንገት አሜሪካንን የጎበኙት ዜሌንስኪ፣ በአሜሪካ ኮንግረስ ንግግር ለማድረግ ሲገቡ አባላቱ ከመቀመጫቸው ተነስተው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ዜሌንስኪ ወደ አሜሪካ ጎራ ያሉት ከሩሲያ ጋር ጦርነት ላይ ላለችው አገራቸው የሚሰጠው ዕርዳታ እንዲቀጥል ለማሳመን ነው።

ዜሌንስኪ እስከአሁን ለተደረገው ዕርዳታ አመስግነው ተጠቃሚዋ ግን ዩክሬን ብቻ አይደለችም ብለዋል።

የምክር ቤቱ ሪፐብሊካን አባላት በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማገዝ በሚቀጥለው ወር የተመደበውን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዳይለቀቅ እንቅፋት ሆነውባቸዋል። አንዳንድ የሪፐብሊካን ዓባላት ዕርዳትው መቆም አለበት ሲሉ ሌሎች ደግሞ እስከ አሁን የወጣው ገንዘብ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ኦዲት እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ዜሌንስኪ ትናንት ለሁለቱም ምክር ቤቶች በጋራ ንግግር ሲያደርጉ፣ በሁለቱም ፓርቲዎች ወገን ያሉ አባላት በተደጋጋሚ ከመቀመጫቸው በመነሳት ሲያጨበጭቡ ተስተውለዋል።

አሜሪካ ለዩክሬን እስከአሁን 50 ቢሊዮን ዶላር ስትሰጥ፣ ተጨማሪ 44.9 ቢሊዮን ዶላር ለማጽደቅ ኮንግረስ በመምከር ላይ ነው።