ጀርመን የአውሮፓ ህብረት ትዊተር ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠየቀች

  • ቪኦኤ ዜና
የትዊተር መለያ ምልክት

የትዊተር መለያ ምልክት

ኢለን መስክ ትዊተርን ጠቅልለው ከያዙ ወዲህ የሚታይ ነው ባለችው “ድንገተኛ” እና “የዘፈቀደ” ውሳኔዎች ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት ትዊተር ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጀርመን ጠይቃለች።

የጀርመን የኢኮኖሚ ሚንስትር ስቬን ጊጎልድ ለአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ “ወላዋይ” ያሉት የትዊተር ፖሊሲ “እጅግ አሳሳቢ” ነው ብለዋል።

ጊጎልድ በጻፉትና በትዊተር ገጻቸውም ባጋሩት ደብዳቤ፣ ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ጉዳዩን ገምግሞ በኅብረቱ የዲጂታል ገበያ ደንብ መሠረት ትዊተር “ጌትኪፐር” የተሰኘው መደብ ውስጥ እንዲገባና ቁጥጥር እንዲደረግበት እንዲወስን ጠይቀዋል።

በኅብረቱ ደንብ መሠረት “ጌትኪፐር” መደብ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች የተለየ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

“የአውሮፓ ኅብረት፣ የገበያ ውድድርን እና የመናገር ነጻነትን ለመጠበቅ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት” ብለዋል ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው።

ኢለን መስክ ትዊተርን በተቆጣጠሩባቸው ባለፉት ስምንት ሣምንታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞች ሲሰናበቱ፣ የታገዱ ገጾች ሲከፈቱ፣ ስለ እርሳቸው የሚጽፉ ጋዜጠኞችን ገጽ ደግሞ አግደዋል።

መስክ ትዊተርን ከያዙ በኋላ ዘረኛና ጥላቻን የሚያንጸባርቁ ጽሁፎችም እየጨመሩ ነው ተብሏል።