የኒው ዮርክ ታይምስ ሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ

  • ቪኦኤ ዜና
አንድ አባል የሰራተኛ ማህበሩ ያደረገውን የስራ ማቆም አድማ የሚደግፍ መፈክር ይዛ በኒው ዮርክ ግዛት ማንሃተን ከተማ በሚገኘው የኒው ዮርክ ታይምዝ ህንፃ ውጪ ቆማ ይታያል - Dec. 8, 2022

አንድ አባል የሰራተኛ ማህበሩ ያደረገውን የስራ ማቆም አድማ የሚደግፍ መፈክር ይዛ በኒው ዮርክ ግዛት ማንሃተን ከተማ በሚገኘው የኒው ዮርክ ታይምዝ ህንፃ ውጪ ቆማ ይታያል - Dec. 8, 2022

የኒው ዮርክ ታይምስ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪና የተሻለ ጥቅማ ጥቅም በመጠየቅ ትናንት ሐሙስ ለ24 ሰዓት የቆየ የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል። አድማው የተጠራው ለ 20 ወራት ከአስተዳደሩ ጋር ሲካሄድ የነበረው ድርድር ውጤት ባለማምጣቱ ነው ተብሏል።

ከ1ሺህ 100 በላይ የሚሆኑ ዘጋቢዎች፣ አርታኢዎች፣ የካሜራ ባለሙያዎችና ሌሎችም የጋዜጣው ሠራተኞች በአውራ ጉዳና ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ውለዋል። ከ40 ዓመታት ወዲህ በጋዜጣ አታሚው ድርጅት የታየ ትልቁ የሠራተኛ አና አሰሪ ጭቅጭቅ ነውም ተብሏል።

“አስተዳደሩ ቶሎ ስምምነት ላይ መድረስ የፈለገ አይመስልም። ባለፈው ሳምንት የተወሰኑ ነገሮችን ተስማምተዋል። ዋናው ጉዳይ የሆነውን ደሞዛችንን በተመለከተ ግን ምንም ሲያደርጉ አይታዩም” ብላላች ኤላ የተባለች የጋዜጣው ሰራተኛ።

ኤላ እንደምትለው ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሠራተኛ ማኅበሩ ያልታቀፉ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሠራተኞች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዘጋቢዎች 9 ሚሊዮን ደንበኞች ላሉት ጋዜጣ በአድማው ቀን ሲሰሩ ውለዋል።

ዋና አዘጋጁ ጆ ካን ለዜና ክፍሉ በጻፉት ኢሜይል፣ የሐሙስ ዕትማቸው ዳጎስ ያለ ቢሆንም ሥራውን ለመጨረስ ግን ከወትሮው ከበድ ይላል ብለዋል።

የኒው ዮርክ ታይምስን ዕትመት ያቋረጠ የሥራ ማቆም አድማ ከዚህ በፊት የተደረገው በእ.አ.አ. 1978 ዓ.ም ሲሆን ለ88 ቀናት ቆይቶ ነበር።