ታይም መጽሔት ዘለንስኪን "የዓመቱ ሰው" ሲል ሰየመ

ቮሎዲሚር ዜለንስኪ

ቮሎዲሚር ዜለንስኪ

ታይም መጽሄት የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን የ2022 “የዓመቱ ሰው” ሲል ዛሬ ሰይሟል።

ዩክሬናውያንን በማነሳሳትና በሩሲያ የተፈጸመውን አፍራሽ ወረራ በመቋቋም ላሳዩት ጀግንነት ዓለም ስላደነቃቸው ነው ሲል መጽሔቱ የተመረጡበትን ምክንያት ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።


ሩሲያ የዩክሬን መዲና ኪቭ ላይ የቦምብ ዝናብ ስታወርድ ከተማዋን ሳይለቁ ሕዝቡን አስተባብረዋል፣ እንዲሁም ከመዲናዋ መልዕክቶችን ለሕዝባቸው አሰራጭተዋል፣ በተጨማሪም በጦርነት ወደ ወደሙት የአገሪቱ ክፍሎች ጉዞ አድርገዋል ሲል መጽሔቱ ዘለንስኪን የመረጠበትን ምክንያት ዘርዝሯል።


ዘለንስኪን የጦርነት ወቅት መሪ መሆናቸውን ያሳዩት፣ ጀግንነት ወደ ሌላ ሰው እንደሚተላለፍ በተግባር በማሳየት ነው ብሏል መጽሔቱ። ይህም የትም ሳይሸሹ በዩክሬን ባሉ የፖለቲካ መሪዎች ላይ ጀግንነት እንዲፈጠር አድርገዋል ሲል መጽሔቱ አክሏል።


ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2021 “የዓመቱ ሰው” የነበሩት፣ ዘንድሮ ትዊተርን የጠቀለሉት የተስላ ኤሌክትሪክ መኪና ባለቤት ኢላን መስክ ነበሩ። ኩባንያቸው በዓለም እጅግ ተቀባይነትን ያገኘ መኪና አምራች መሆናቸውም ተገልጿል።


ታይም መጽሄት የዓመቱ ሠው የሚለውን ስያሜ መስጠት የጀመረው እ.አ.አ ከ1927 ጀምሮ ነው።

እ.አ.አ ጥር 6 ቀን 1936 ዓ/ም መጽሔቱ የኢትዮጵያውን ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “የዓመቱ ሰው” ሲል መሰየሙ ይታወሳል።