ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ መፈንቅለ-መንግስቶችን ያስተናገደው የምዕራብ አፍሪካ ክልል አገራት መሪዎች “ደህንነትንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓትን ለመጠበቅ” የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመመስረት ትናንት እሁድ ተስማማተዋል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኤኮዋስ) ተብሎ የሚጠራው የቀጠናው ማኅበር፣ በአባል አገራት ውስጥ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለመስራት እንደሚጥር አስታውቋል።
“የመፈንቅለ-መንግስት ቀለበት” ተብሎ መጠራት የጀመረው የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ መፈንቅለ-መንግስቶች ሲካሄዱበት ሰንብቷል።
ኤኮዋስ ባወጣው የጋራ መግለጫ አባል አገራቱ ደህንነትን ለማረጋጋጥ፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንዲሁም በአባል አገራት ውስጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚረዳ አንድ ቀጠናዊ ጦር ለመገንባት ወስነዋል።
የኢኮዋስ አገራት መሪዎች በተጨማሪም በማሊ የታገቱትን 46 የአይቮሪ ኮስት ወታደሮችን በተመለከተ ያላቸውን ስጋት ገልጸው፣ የማይለቀቁ ከሆነ “አንዳንድ እርምጃዎች የመውሰድ መብታችንን እንጠቀማለን” ብለዋል በመግለጫቸው።
በጊኒ ሁሉንም አካታች ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ሲያደርጉ፣ በቡርኪና ፋሶ ያለው ሁኔታ ደግሞ እንደሚያሳስባቸው የኤኮዋስ መሪዎቹ ጨምረው አስታውቀዋል።