ተመድ በሰብዓዊ ቀውስ ለተጎዱ ህፃናት 10.3 ቢሊየን ዶላር ጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና

ፋይል - በፓኪስታን ላልባግህ ሲንዳ ግዛት የጎርፍ አደጋ ያፈናቀላቸው ህፃናት የምግብ ርዳታ ለመቀበል ሲጠብቁ - Sept. 13, 2022.

በከባቢ አየር ለውጥና በሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትን 110 ሚሊዮን ሕጻናት ለመታደግ 10.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።


“በዓለማችን ታሪክ አይተነው የማናውቀው ብዛት ያላቸው ሕጻናት የሰብዓዊ እርዳታ ይሻሉ” ብለዋል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካትሪን ረስል።


በሰብዓዊ ቀውስ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት ችግር ውስጥ ለውደቁ 173 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋል ሲል ድርጅቱ ዛሬ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 110 ሚሊዮኑ ሕጻናት መሆናቸውንም አስታውቋል።


የከባቢ አየር ለውጥ ሁኔታውን እንዳባባሰውና ባለፉት 10 ዓመታት የታየው የአየር ሁኔታ እስከ አሁን ከነበረው የበለጠ ሞቃታማ ተብሎ የተመዘገበ መሆኑን እንዲሁም ባለፉት 30 ዓመታት ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር የተገናኙ አደጋዎች በሶስት እጥፍ መጨመራቸውን የሕጻናት አድን ድርጅቱ ባወጣው ጥሪ ላይ ተቁሟል።