በጣሊያን በደረሰ የመሬት መንሸራተት ስምንት ሰዎች ሞቱ

  • ቪኦኤ ዜና

በጣሊያን የመዝናኛ ደሴት በሆነው ኢሺያ ደሴት ላይ የደረሰው የመሬት መንሸራተት

በጣሊያን ኢሺያ ደሴት የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።

በደሴቱ ከሚገኙ ስድስት ከተሞች አንዱ በሆነው ካሳሚቾላ ቴርም በደርሰው የጭቃ ማዕበል ቢያንስ አንድ ቤት የተዋጠ ሲሆን በርካታ መኪናዎችን ገፍቶ ወደ ባህር ከቷቸዋል። በአንደኛው መኪና ውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎችን ማዳን ተችሏል።

እስካሁን ባለው መረጃ አንድ አዲስ የተወለደ ህፃንን ጨምሮ 13 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። ባለስልጣናት በደሴቱ ሌሎች ከተሞች የሚኖሩና የመሬት መንሸራተት ጉዳት ያላደርሰባቸው ሰዎች በቤታቸው እንዲቀመጡ ሲሉ ጠይቀዋል።

ኢሺያ በእሳተ ገሞራ የተፈጠረች በታይረኒያ ባህር ውስጥ የምትገኝ ደሴት ስትሆን ከኔፕልስ በ30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። እ.አ.አ በ2017 በካሳሚቾላ ቴርም የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል።