የሲ አይ ኤ ኃላፊ ከፑቲን የስለላ ኃላፊ ጋር ተገናኝተው ተወያዩ

የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ

የዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ ድርጅት ሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ፣ ዊሊያም በርንስ፣ ሩሲያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ብትጠቀም ሊከተል የሚችለውን መዘዝ ለፕሬዚዳንት ፑቲን የውጭ ስለላ ድርጅት ኃላፊ፣ ሰርጌ ናሪሽኪን ለማስረዳት በቱርክ እንደሚገኙ የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡

ዩክሬን ሩሲያን ከወረረችበት ካለፈው የካቲት ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ ፊት ለፊት ሲገናኙ ዛሬ ሰኞ በአንካራ የተደረገው የመጀመሪያቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የሲ አይ ኤው ዳይሬክተር “ምንም ዓይነት ድርድር እያካሄዱ አይደለም:፡ስለ ዩክሬኑ ጦርነትም እልባት እንዲሰጠውም እየተነጋገሩ አይደለም” ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

“ሩሲያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ብትጠቀም የሚያስከትለውን መዘዝ እና ስትራቴጂካዊ ወደ ሆነ አለመረጋጋት ሊያድግ የሚችለውን አደጋ አስመልክቶ መልዕክት እያስተላለፉ ነው” ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ “በተጨማሪም በግፍ የታሰሩ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎችን ጉዳይ ያነሳሉ” ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

በሩሲያ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የነበሩት በርነስ እኤአ በ2021 መጨረሻ ሞስኮ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ የምታደርገውን የሠራዊት ግንባታ አስመልከቶ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተላከውን ማስጠንቀቂያ ለፕሬዚዳንት ፑቲን ማድረሳቸው ተመልክቷል፡፡

በዩክሬን ስላለው ጦርነት እልባት ለመስጠት ምንም ዓይነት ድርድር አለማድረጋቸውን የገለጹት ቃል አቀባዪ ጉዞውን አስመልክቶ በቅድሚያ ለዩክሬን ማብራሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለው “ መሠረታዊ የሆነ መርሃችንን አጥብቀን እንከተላለን ፤ ዩክሬን በሌለችበት ስለ ዩክሬን የሚደረግ አንዳች ነገር አይኖርም” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡