ዓሊ ብራ አረፈ

  • ቪኦኤ ዜና

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ረዘም ላሉ ዓመታት ከነገሡት ጥቂት ድምጻዊያን አንዱ የሆነው አንጋፋው የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዓሊ መሐመድ ብራ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አንጋፋው ድምጻዊ ዛሬ ጥቅምት 27፣ 2015፣ ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ባጋጠመዉ ሕመም ምክንያት ላለፉት ወራት በአዳማ ጄኔራል ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በሗላ ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት እና የሞያ አጋሮቹ እንደዚሁም አድናቂዎቹ በአንጋፋው ድምጻዊ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል ።


በርካቶችም አርቲስቱ በሕክምና ሲረዳ ወደቆየበት የአዳማ ጀኔራል ሆስፒታል ድረስ በአካል በመሄድ ሐዘናቸውን እና ያላቸዉን ክብር በመግለፅ ላይ ናቸዉ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም የአርቲስቱን ሞት አስመልክቶ የሐዘን መግለጫ ያወጣ ሲሆን በክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የተዋቀረ የቀብር ስነስርዓቱን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ስራ መጀመሩንም አመልክቷል።

የአንጋፋውን ድምጻዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ተከትሎ የሚኖሩ ቀጣይ መረሃግብሮችን መዘገባችንን፣ እንደዚሁም ሕይወትና ስራዎቹን መዘከራችንን እንቀጥላለን።