በምግብ ድልድል ምክንያት በማላዊ የሚገኙ ስደተኞች የተመድ መኪናን ያዙ

  • ቪኦኤ ዜና

በማላዊ ዴዛሌካ መጠለያ ጣቢያ የምግብ ድልድሉን የተቃወሙ ስደተኞች የዓለም ጤና ፕሮግራምን መኪና ተቆጣጥረዋል። መኪናውን የሚለቁት ጥያቄያቸው ከተመለሰ መሆኑን ገልፀዋል።

ማላዊ በሚገኘው ዴዛሌካ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ እና ከምግብ ድልድል መዝገብ ላይ የተሰረዙ ስደተኞች ተቃውሞአቸውን ለማሰማት የዓለም ምግብ ድርጅት መኪናን በቁጥጥር ስር አውለዋል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም በየካቲት ወር በቂ የገንዘብ ድጋፍ ባለመኖሩ፣ 600 የሚጠጉ የስደተኛ ቤተሰቦች ራሳቸውን ችለዋል በሚል የምግብ ራሽን ከሚቀበሉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አውጥቷቸው ነበር። ነገር ግን በአብዛኛው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈናቀሉት ሰዎች አሁን በምግብ እጦት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም ከብሩንዲ መፈናቀሉን የሚገልፀው ንዳይዝ ኤሊውዴ ቤተሰቡን መመገብ እንዳልቻለ እና በከፍተኛ ሁኔታ መራቡን ይገልፃል። በአሁኑ ወቅት ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙት ስደተኞች የዓለም ምግብ ድርጅትን መኪና እንደተቆጣጠሩ ሲሆን ለስብሰባ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የነበሩት የድርጅት ሰራተኞች ወዲያው መውጣት አለመቻላቸው ተገልጿል። ሆኖም ከሰዓታት በኃላ ያለምንም ሁከት ሰራተኞቹ እንዲወጡ ተደርገዋል።

መኪናውን የተቆጣጠሩት ስደተኞች መኪናውን የሚለቁት የምግብ ተቋሙ በድጋሚ በምግብ ድልድሉ ውስጥ የሚያገባቸው ከሆነ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።