በሊባኖስ ፍልሰተኞችን ይዞ በሰጠመ ጀልባ 89 ሰዎች ሞቱ

  • ቪኦኤ ዜና

ስደተኞችን ይዞ በሰጠመው ጀልባ ከሞቱት መካከል የ24 አመቱን አብዱል አል አብዱል አስክሬን የተሸከሙ ሀዘንተኞች በስደተኛ ፍልስጤሞች መጠለያ ጣቢያ በተካሄደው የቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ መፈክር ሲያሰሙ 

በሊባኖስ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በሶሪያ አቅራቢያ በሰጠመ ጀልባ የሞቱ ስደተኞችን ለማሰብ ፀሎት አካሂደዋል።

በሶሪያ የባህር ዳርቻ፣ ታርተስ የተሰኘች ከተማ በሚገኝ አል-ባዝል የተሰኘ ሆስፒታል ሀላፊ ዛሬ በሰጡት ቃል በሰጠመው ጀልባ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 89 የደረሰ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎች ደግሞ በተቋሙ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የሊባኖስ ጦር በበኩሉ ይህን አደገኛ ጉዞ በማቀነባበር የተጠረጠረውን ግለሰብ መያዙን አስታውቋል።

አደጋው የሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ፍልስጤም ስደተኞች የተሻለ ስራ እና የተረጋጋ ኑሮ ፍለጋ ባህር አቋርጠው አውሮፓ ለመግባት በሚያደርጉት ሙከራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሞተበት መሆኑ ተገልጿል።

የሊባኖስ ብሔራዊ ገንዘብ የምንዛሬ መጠን መውረዱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስራቸውን ያጡ ሲሆን ሀገሪቱ አንድ ሚሊየን ከሚጠጉ የሶሪያ ስደተኞች በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም ስደተኞችንም አስጠልላለች።