በአፍሪካ ቀንድ የቀጠለው ድርቅ የረሃብ ቀውሱን አባብሶታል

  • ቪኦኤ ዜና

ፋይል - ድርቁን ለመሸሽ ከታችኛው የሸበሌ አካባቢ የተሰደደችው የ25 አመቷ ኑናይ መሀመድ ከሞቃዲሾ ከተማ ወጣ ብሎ በምትኖርበት ግዜያዊ መጠለያ፣ በምግብ እጥረት የተጠቃውን የአንድ አመት ልጇን አቅፋ ይታያል።

በአፍሪካ ቀንድ ከ9 ሚሊየን በላይ እንሳስትን የገደለው ድርቅ ከ37 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በረሃብ እያሰቃያቸው መሆኑን የእርዳታ ሰጪ ቡድኖች አስታውቀዋል። በተለይ በሱማሊያ ያለው ሁኔታ የከፋ መሆኑ እና በዚህ አመት ብቻ ከ700 በላይ ህፃናት በምግብ እጥረት መሞታቸውም ተገልጿል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለው ተፅእኖ እና ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያካሄደችው ወረራ በዓለም ዙሪያ ያለው የረሃብ ሁኔታ ለመባባሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ባለሙያዎች የገለፁ ሲሆን በተለይ ግን በአፍሪካ ቀንድ ለአምስተኛ ተከታታይ ወቅት ዝናብ ባለመጣሉ እ.አ.አ በጥቅምት 2020 ዓ.ም የጀመረው ድርቅ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን አስምረውበታል።

ኬር ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ባወጣው መረጃም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚገኙ ከ36 ሚሊየን በላይ ሰዎች እጅግ አስከፊ ለሆነ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።

የረሃብ አደጋው በተለይ እናቶች እና ህፃናትን የበለጠ ማጥቃቱን የገለፀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ በአሁኑ ወቅት በኬንያ 942 ሺህ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናት እና 135 ሺህ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች በከፍተኛ የምግብ እጥረት በሽታ መጠቃታቸውን እንዲሁም አስቸኳይ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም ልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ -ኤ አይ ዲ) በአፍሪካ ቀንድ ሰብዓዊ ርዳታ ለመስጠት ከ2020 ጀምሮ 1.3 ቢሊየን ዶላር የሰጠ ሲሆን በዚህ ሳምንት በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለም ዙሪያ የተከሰውን ረሃብ ለመዋጋት 10 ቢሊየን ዶላር እንደሚሰጡ ቃል ገበተዋል። ከዚህ ገንዘብ ምን ያክሉ ለአፍሪቃ ቀንድ እንደሚውል ግን አልታወቀም።