ከቦረና ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው የዞኑ ሌሎች ሦስት ወረዳዎች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፍ እንደተነፈጋቸው እየተናገሩ ነው።
ዱብሉቅ ወረዳ ውስጥ የተጠለሉ አንድ ሺህ 500 በላይ አባወራዎች በቂ ምግብና ውኃ እንደማያገኙና የፅዳትና ንፅህና ጥበቃ ችግርም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ተፈናቃዮቹ ዱብሉቅ ውስጥ ለስድስት ወራት መቆየታቸውን የገለፁት የወረዳው አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ባልደረባ አቶ ዴበኖ ሳራ ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተፈናቃዮቹ ችግር የከበደ መሆኑን እንደሚረዱ የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉዮ ጨርፊ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ገልሞ ዳዊት ሰሞኑን ወደዚያው ተጉዞ ያለውን ሁኔታ ተመልክቷል። ተፈናቃዮቹንና ባለሥልጣናቱን አነጋግሮ ዘገባ አሰናድቷል።