የሩዋንዳ ወታደሮች እአአ ካለፈው 2021 ህዳር ወር እስካለፈው ሀምሌ በነበረው ጊዜ ምስራቃዊ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ ወታደራዊ ኦፐሬሽን ማካሄዳቸውን እና፣ ሩዋንዳ ኤም 23 የተባለው ታጣቂ ቡድን ምስራቅ ኮንጎ ውስጥ ጥቃቱን እንዲያጠናክር መርዳቷን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አግኝተናል ሲሉ የተመድ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪ ቡድን ይህን ያለው ሮይተርስ ዛሬ ሀሙስ ባገኘው ሚስጥራዊ ሪፖርቱ ሲሆን ሩዋንዳ ውንጀላዎቹን አስተባብላለች።
የኤም 23 ታጣቂዎች ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በኮንጎ የጦር ሠራዊት ላይ በአስር ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማያውቅ ደረጃ ጠንካራ ጥቃት አካሂዷል።
በርካታ ሲቪሎች የገደለ ሲሆን ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ ወሰን አካባቢ ያሉ ከተሞችን በመቆጣጠር ብዙ ሺህ ሰዎችን ከመኖርያቸው አፈናቅሏል።