ፔለሲ የእሥያ ጉብኝታቸውን ጀመሩ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔለሲ

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔለሲ የሲንጋፖር የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን ዛሬ ጀምረዋል።

አምስት የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እንደራሴዎች ያሉበትን ቡድን በመምራት የተንቀሳቀሱት አፈጉባዔ ፔለሲ ማሌዢያና ደቡብ ኮርያንም እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ሰሞኑን አፈጉባዔዋ ቻይና እንደግዛቷ የምትቆጥራትን ታይዋንን ሊጎበኙ ይችላሉ የሚሉ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ከወጡ በኋላ አሜሪካና ቻይና የተጋጋለ ፍጥጫ ውስጥ ቢገቡም ጉብኝታቸው ታይዋንን ይጨምር እንደሆን ግልፅ አይደለም።

በሲንጋፖር ፔለሲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ሴይን ሎን እና ከፕሬዚዳንት ሃሚላ ያኮብ ጋር መገናኘታቸውንና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋርም እንደሚገናኙ የሃገሪቱ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

የጉብኝታቸው ዓላማ ለአካባቢው ሃገሮች የአሜሪካን የማይናወጥ ድጋፍ ለማረጋገጥ እንደሆነ ፔለሲ ትናንት የተናገሩ ሲሆን ሁለቱን ልዕለ-ኃያላን ፍጥጫና የጋለ ንግግር ውስጥ የከተታቸውን የታይዋን ጉብኝት ጉዳይ ግን አላነሱም።

ፔለሲ ታይዋንን ለመጎብኘት “የቅድሚያ ብጤ” የሚባል ዕቅድ እንደነበራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ዓርብ ሲዘግቡ ነበር።

ፔለሲ እራሳቸውም ታይዋንን ሊጎበኙ የመቻላቸውን ነገር በገደምዳሜ ተናግረው ነበር።

ቢሯቸው የደኅንነት ጥንቃቄን ሰበብ በማድረግ ታይዋንን ስለመጎብኘት አለመጎብኘታቸው ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥቧል።