የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በስልክ ተገናኝተው አሜሪካ በሩሲያ በእስር ላይ የምትገኘውን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግሪነርን እና የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል አባል ፓውል ዌለን እንድትለቅ ያቀረበችውን ሐሳብ እንድትቀበል ጠይቀዋል።
የስልክ ጥሪው ሩሲያ በየካቲት ወር በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመች ወዲህ ሁለቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ንግግር ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ በሁለቱ አማሪካውያኖች ምትክ ህገወጥ መሳሪያ በማዘዋወር የተፈረደበትን ሩሲያዊ ቪክቶር ባውት ወደ ሞስኮ እንደምትልክ አስታውቃለች።
አሜሪካ ያቀረበችውን የእስረኛ ልውውጥ ጥያቄ ተከትሎ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገለፀው ነገር ባይኖርም አሜሪካ 'ሰላማዊ ዲፕሎማሲ' አልተከተለችም በሚል ግን ቁጣውን ግለጿል።