የአል-ቃኢዳ ተባባሪ በማሊ ወታደራዊ ተቋም ላይ ለደረሰው ጥቃት ሀላፊነት ወሰደ

  • ቪኦኤ ዜና
የማሊ ወታደሮች ካቲ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ሲገቡ ህብረተሰቡ በሆታ ተቀብሏቸዋል

የማሊ ወታደሮች ካቲ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ሲገቡ ህብረተሰቡ በሆታ ተቀብሏቸዋል

ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን በማሊ ወታደራዊ ተቋም ላይ ለደረሰው ጥቃት ሀላፊነቱን እንደሚወስድ አስታወቀ። ቡድኑ ጥቃቱን ያደረሰው መንግስት ከሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ለፈጠረው ትብብር ምላሽ ለመስጠት መሆኑንም አስታውቋል።

ከዋና ከተማው ባማኮ 15 ኪሎሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው ወታደራዊ ስፍራ ላይ የደረሰው ጥቃት የአንድ ወታደር ህይወት ሲያጠፋ ስድስት ሰዎችን አቁስሏል። ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ ቦንቦችን በመጠቀም ጥቃት ካደረሱት ውስጥ ሰባቱ ወዲያው ሲገደሉ፣ ስምንቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የማሊ ጦር አስታውቋል።

የአል-ቃኢዳ ተባባሪ የሆነው 'ጃማት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል ሙስሊም' ባወጣው መግለጫ "የባማኮ መንግስት ቅጥረኛ ወታደሮችን በመጠቀም ንፁሃን ሰዎችን ለመግደል መብት ካለው እኛም እናንተን ኢላማ የማድረግና የማጥፋት መብት አለን" ሲል አስታውቋል።

ዋግነር የተሰኘው ቡድን በማሊ እንደሚገኝ የሩሲያ መንግስት እውቅና ቢሰጥም፣ የማሊ መንግስት ከሩሲያ ጦር የተላኩ አሰልጣኞች እንጂ የግል የፀጥታ ቅጥረኞች አለመሆናቸውን አመልክቷል።