ባይደን ፅንስ ለማቋረጥ መብት ከለላ የሚሰጥ ትዕዛዝ ሊፈርሙ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፅንስን ለማቋረጥ መብት ከለላ የሚሰጥ አስፈፃሚ ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

ፕሬዚዳንቱ እርምጃውን የሚወስዱት የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “የሮ እና የዌድ ሙግት ጉዳይ” እየተባለ ሲጠራ የቆየውንና ፅንስን ለማቋረጥ መብት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ፌደራልና ህገመንግሥታዊ ከለላ ሲሰጥ የቆየውን ህግ በመሻሩ ነው።

ባይደን አንዳች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ከደጋፊዎቻቸው በተለይም ፕሮግሬሲቭስ (ተራማጆች) ከሚባሉት ፖለቲከኞች ግፊት ሲደረግባቸው ሰንብቷል።

ፕሬዚዳንቱ በምግብና በመድኃኒት አስተዳደሩ ተቀባይነት ያለውን “የህክምና ፅንስ ማቋረጥ” ተደራሽነትን እንዲጠብቅና እንዲያሰፋ ለጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው መመሪያ እንደሚሰጡ ዋይት ሃውስ አክሎ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

በተጨማሪም ሴቶች የድንገተኛ ህክምና እርዳታ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ በመዋለጃ አካል ውስጥ የሚቀመጡትን ጨምሮ የእርግዝና መካለከያ አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን እንዲያረጋግጥም ፕሬዚዳንቱ የጤና ሚኒስቴሩን እንደሚያዝዙ ቤተ መንግሥቱ ገልጿል።

የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግና ዋይት ሃውስ ነገረፈጅ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችንና ሌሎችም ድርጅቶችን ሰብስበው ፅንስ ማቋረጥ ለሚፈልጉና አገልግሎቱንም ለሚሰጡ የህግ ምክር እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሚያዘጋጁም ተዘግቧል።