የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት ሻረ

Your browser doesn’t support HTML5

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት ሻረ

ወግ አጥባቂዎች በአብላጫ የተቆጣጠሩት የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እአአ በ1973 የፅንስ ማቋረጥ ህገመንግስታዊ መብት ሆኖ እንዲፀድቅ ያስቻለውንና ሮይ እና ዌድ በመባል የሚታወቀውን የፍርድ ሂደት ሽሮታል። ስድስት ለ3 በሆነ ድምፅ ባለፈው ሳምንት የተላለፈው ይህ ውሳኔ የመጣው፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሳሪያ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማላላት ውሳኔ ካሳለፈ በኃላ ሲሆን የአሜሪካ ምክርቤት በመሳሪያ ቁጥጥር ዙሪያ ያሳለፈውንና በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተፈረመውን ውሳኔ የሚፃረር ነው። የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ አራሽ አራብሳዲ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዙሪያ ያጠናቀረው ነው።

ባለፈው ሳምንት አርብ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በህገ መንግሥት ተሰጥቶ የነበረውን ፅንስ የማቋረጥ መብት መሻሩን ተከትሎ ቅዳሜ እለት ተቃዋሚዎች ዋሽንግተን ወደሚገኘው ፍርድ ቤት አቅንተዋል።

ከ50 አመት በላይ ያስቆጠረውና በሮይ እና ዌድ መሀከል የተደረገው የፍርድ ቤት ክርክር ላይ ተመርኩዞ የሴቶችን የመምረጥ መብት የሚያስከብረው ህግ መሻር ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል። አርብ እለት አሪዞና ክፍለግዛት በሚገኘው የምክር ቤቱ ህንፃ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ በሁለቱም ወገን የሚከራከሩ የመብት አቀንቃኞች ያካሄዱት ሰልፍ የህግ አወጣቱን ሂደት ለተወሰነ ግዜ አስተጓጉሎት ነበር። ሰልፈኞቹ በመስታወት የተሰራውን የህንፃውን በር መደብደብ ሲጀምሩ ህግ አስከባሪዎች በተሰበሰበው ህዝብ ላይ አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱንም የሀገር ውስጥ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በርግጥ የሮይ እና ዌድ ህግ መሻር ማለት በመላ ሀገሪቱ ፅንስ የማቋረጥ እግድ ተጥሏል ማለት አይደለም። ሆኖም ውሳኔው ለተለያዩ ክፍለ ግዛቶች መልዕክት ያስተላልፋል። በሪፐሊካኖች የሚመሩ አብዛኞቹ ክፍለግዛቶች በግዛታቸው ፅንስ ማቋረጥ እንዲታገድ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው - ፅንሱ የተፈጠረው በአስገድዶ መድፈር፣ በዘመዳሞች መሀከል በተደረገ ግንኙነት ወይም ለእናት ህይወት በሚያሰጋ መልኩ ቢሆንም እንኳን።

የአሜሪካ የቴሌቭዥን ጣቢያ ከሆነው ኤቢሲ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የደቡብ ዳኮታ ሪፐብሊካን ገዢ ክሪስቲ ኖውም ስለጉዳዩ ተጠይቀው ይህን ብለዋል።

"የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ አንድ ጥሩ ነገሩ ክፍለግዛቶች የየራሳቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ ስልጣኑን መስጠቱ ነው። ስለዚህ አሁን ውሳኔውን ተከትሎ ቀጣዩ የእያንዳንዱ ግዛት እና የየግዛቱ ህግ አውጪ ነው የሚሆነው። እናም ህዝቡ ህጉ በሚኖርበት አካባቢ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ከመረጣቸው ወኪሎቹ ጋር ይነጋገራል።"

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በፅንስ ማቋረጥ ዙሪያ ያሳለፈው ውሳኔ ሌሎች ተመሳሳይ አነጋጋሪ ውሳኔዎችን ተከትሎ የመጣ ሲሆን ከነዚህ አንዱ በሀገሪቱ በተከታታይ የተካሄዱ የመሳሪያ ጅምላ ግድያዎችን ተከትሎ የመሳሪያ ቁጥጥር እንዲደረግ ፓርቲዎቹ ያለልዩነት ድጋፍ እያደረጉ ባሉበት ወቅት ቁጥጥሩ እንዲላላ የተወሰነው ውሳኔ ነው።

የማሳቹሴትስ ዲምክራቲክ ተመራጭ ሴናተር ኤሊዛቤት ዋረን ከኤቢሲ ቴሌቭዥን ጣቢያ ሲናገሩ ይህን ብለዋል።

"ፍርድ ቤቱ ተዓማኒነቱን አጥቷል። በመሳሪያ ቁጥጥር እና በምርጫ ዙሪያ ካሳለፉት ውሳኔ በኃላ ቀርቶ የነበረውን ትራፊ እምነት አቃጥለውታል። በቃ በሮይ እና ዌድ ውሳኔ ላይ ባሳለፉት ውሳኔ የመጨረሻውን ጠብታ ወስደው እሳት ለኩሰውበታል።"

የሮይ ውሳኔ ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪም ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያሳድር ነው። ለተመሳሳይ ፆታዊ ግንኙነት ድጋፍ በማድረግ በፓሪስ በተካሄደ ሰልፍ ላይ አንዳንድ አቀንቃኞች ፈረንሳይ የፅንስ ማቋረጥ መብትን ህገመንግስታዊ እንድታደርግ ጠይቀው ነበር። ልክ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ፈረንሳይም ለግማሽ መዕተ አመት የሚሆን ግዜ የፅንስ ማቋረጥ መብትን ስታስከብር ቆይታለች። ከሰልፈኞቹ አንዷ ማሪአ ተሌስካ ነች።

"የሆነ የወንድ የበላይነት የነገሰበት ብሄራዊ ስሜት እየተሰራጨ ያለ ይመስለኛል። ነገር ግን እነደዚህ አይነት ወግ አጥባቂ ጠቅላይ ፍርድ ቤትበዩናይትድ ስቴትስ በመኖሩ መብታችንን ጠቅልለው እየወሰዱት ነው። እንደ ወጣት ሴት በሰውነቴ ላይ የምፈልገውን የማድረግ መብት ኖሮኝ ነው የኖኩት። አሁን ሴት ልጄ ወደ አሜሪካ ብትመጣ ይሄ መብት አይኖራትም ማለት ነው። ይሄ ልብ የሚሰብር ነገር ነው።"

በሌላ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ የፅንስ ማቋረጥ የሚቃወሙ አቀንቃኞች ለአስርት አመታት የኖረው የፍርድ ሂደት በመታገዱ ውሳኔው አስደስቷቸዋል። ከነዚህ አንዷ ሌክሲ ሆል 'ክርኤትድ ኢኳል' የተሰኘ ፅንስ ማቋረጥን የሚቃወም ድርጅት ውስጥ አቀንቃኝ ስትሆን ለአሶስዬትድ ፕሬስ ይህን አስተያየት ሰጥታለች።

"ይሄ ለኛ እጅግ የሚያስደስት ጊዜ ነው። ሮይ እና ዌድ የተባለውን ውሳኔ የሚቀለብሰው ውሳኔ ሲተላለፍ ሰማኒያ የምንሆን የመኖርን መብት የምንደግፍ ሰዎች ሰዎች አንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስበን ነበር። በጣም ነው የተደሰትነው። ስራው መቀጠል እንዳለበት እና ገና ብዙ የሚሰራ ስራ እንዳለም እናውቃለን።"

የሮይ እና ዌድ የተሰኘው የፅንስ ማቋረጥን መብት የሚያስከብረው ውሳኔ አርብ እለት ከተሻረ በኃላ አስር የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥ እንዲታገድ አድርገዋል።