ጀርመን የቡድን ሰባት ባለጸጋ እና ዴሞክራሲያዊ አባል ሃገራት መሪዎች ተቀበለች

የቡድን አባል ሃገራት መሪዎች በጀርመን አቀባበል ሲደረግላቸው

የቡድን ሰባት አባል ሃገራት ስብስባ ላይ ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ እና ዩናይትድ ስቴትስ የሚሳተፉ ሲሆን ስብሰባው በጀርመን ባቫሪያን አልፕስ በሚገኝ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተካሂዷል።

ይህ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የመሪዎች ስብሰባ የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ጥላ ያጠላበት ሲሆን የፖለቲካ ተንታኞች በቀጣዮቹ ቀናት ሃገራቱ እጅግ ትልቅ የሚባል ድጋፍ ለዩክሬን እንዲያደርጉ ይጠበቃል ሲሉ ተንብየዋል።

የጀርመኑ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሹልዝ በቅርቡ በሃገራቸው ፓርላማ ፊት ቀርበው፣

“ይሄ የመሪዎች ስብሰባ የሰሜን አትላንቲክ የቃልኪዳን ሃገራት ኔቶ እና የቡድን ሰባት አባል ሃገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጣመራቸውን ብቻ ሳይሆን የዓለም ዴሞክራሲዎች በሙሉ ርሃብ እና ድህነትን ለመዋጋት በአንድነት እንደቆሙት ሁሉ የሩሲያውን ፕሬዘዳንት ቩላድሚር ፑቲንን የኢምፔሪያሊዝም ሃሳብም ለመዋጋት በአንድነት መቆማቸውን ነው።” ብለዋል።

በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብም በዓለም አቀፍ የምግብ እና የኃይል ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ፈጥሯል።

ይህ በጀርመን የሚካሄደው ስብሰባ እንዳበቃም የቡድን ሰባት ሃገራት መሪዎች በኔቶ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለማካፈል ወደ ስፔን ማድሪድ ያመራሉ።