የ”ኢትዮፎረም” አዘጋጅ የነበረው ያየሰው ሽመልስ ከእስር ተፈታ

ያየሰው ሽመልስ፣ መዓዛ መሐመድም

- ባለፈው ዓርብ ከእስር እንድትፈታ የተወሰነላት መዓዛ መሐመድም፣ አስፈላጊ ሂደቶችን አጠናቃ በዛሬው ዕለት ተፈታለች

”ኢትዮፎረም” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ የነበረው ያየሰው ሽመልስ የ10 ሺህ ብር ዋስ በማስያዝ ዛሬ ከእስር መፈታቱን ጠበቃው ታደለ ገብረመድህን አረጋግጠዋል፡፡

ዛሬ ሰኔ 13/2014 ዓ.ም. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፣ በሰጠው ውሳኔ መሰረት ነው ያየሰው ዋስትናውን በማስያዝ ከእስር ተለቀቀው፡፡

በዛሬው ችሎት መርማሪ ፖሊስ በያየሰው ላይ ያላጠናቀቀው የምርመራ ሂደት መኖሩን በማሳወቅ፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁን የገለጹት ጠበቃ ታደለ፣ የፖሊስን ጥያቄ በመቃወም መከራከራቸውን እና የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ በስተመጨረሻ ያየሰው በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተከትሎም ቤተሰቦቹ የዋስትናውን ገንዘብ አስይዘው፣ ከ ግንበቦት 18/2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበረው ያየሰው ሽመልስ ከሰዓት በኋላ ተፈትቶ ወደ ቤቱ መግባቱንም አክለው ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት ባለፈው ዓርብ ሰኔ 10/2014 ዓ.ም በዋስትና ከእስር እንድትፈታ የወሰነላት የ “ሮሃ” ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መዓዛ መሐመድም ዛሬ መፈታቷን ጠበቃዋ ሄኖክ አክሊሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ የስር ፍርድ ቤት ግንቦት 30 የተሰጣት የ10 ሺህ ብር ዋስትና ተፈጻሚ እንዲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓርብ ከወሰነ በኋላ፣ ለመፈታት የሚያስፈልጉ አስተዳደራዊ ሂደቶችን ዛሬ አጠናቃ መለቀቋን ነው ጠበቃው የገለጹት፡፡ መዓዛ መሐመድ ግንቦት 20/2014 ዓ.ም ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው፡፡

ከመዓዛ ጋር በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይግባኝ አቤቱታው የታየለት የ“ገበያኑ” ዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ፣ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ፀንቶ በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ በተወሰነው መሰረት በዕለቱ ሂደቱን አጠናቆ መፈታቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሁለቱም የሚዲያ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው ነው፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሌሎች የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል መስከረም አበራ ረቡዕ ሰኔ 8/2014 ዓ.ም በ30 ሺህ ብር ዋስ የተለቀቀች ሲሆን፣ በተመስገን ደሳለኝ ላይ ደግሞ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት መታዘዙ ይታወሳል፡፡