ከሱዳን ህዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የፖለቲካ ብጥብጥ የምግብ ዋጋ መናር እና የአየር ንብረት መለዋወጥ ተደማምሮ ለምግብ ቀውስ ያጋለጠው መሆኑን የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የምግብ እና የግብርና ድርጅቱ ባወጡት የጋራ ሪፖርት በጠቅላላው የሱዳን 18 ክፍላተ ሀገር አስራ አምስት ሚሊዮን ሰዎች አጣዳፊ የምግብ ቀውስ ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሱዳን ተወካይ ኤዲ ሮው በሰጡት ቃል፣
"ግጭት፣ የአየር ንብረት መዘበራረቅ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ቀውሶች የዋጋ መናር እንዲሁም በቂ የግብርና ምርት አለመመረቱ ተደማምሮ በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ሰዎችን የጸና ረሃብ እና ድህነት አጋልጧል" ሲሉ አስረድተዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ በምታካሂደው ጦርነት አስቀድሞም የነበረውን ከባድ የኢኮኖሚ ችግር አባብሶታል። ረሃቡ እንዳይባባስ ለመከላከል እና የህዝቡን ህይወት ለማትረፍ አሁኑኑ እርምጃ መውስድ ይኖርብናል ሲሉም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተጠሪው አሳስበዋል።