በዩናይትድ ስቴትስ ሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ሚኒያፖሊስ ውስጥ፣ እኤአ ግንቦት 25/2020፣ በፖሊስ የተገደለውን ጥቁሩን ጆርጅ ፍሎይድ ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር፣ እስከ ቅዳሜ የሚዘልቀው ዝግጅት፣ ትናንት ረቡዕ በሻማ ማብራት ስነ ሥርዓት መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ማህበረሰባዊ አንቂዎች ከሻማ ማብራቱ በተጨማሪ ሴንትፖል በሚገኘው በአገረ ገዥው መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ሰልፍ ማድረጋቸውን የአሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ዝግጅቱ ዛሬ ሐሙስም የሚቀጥል ሲሆን፣ ከፖሊስጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጡ የጥቁር አሜሪካውያን ቤተሰቦችና ወዳጆች መሳባሰብ እንደሚካሄድ ተዘግቧል፡፡
ነገ ዓርብም እንዲሁ፣ ጆርጅ ፍሎይድ በተገደለበት ስፍራ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት፣ በማግስቱ ቅዳሜ የሙዚቃ ትርኢት የሚቀርብ መሆኑም ተመልክቷል፡፡