ሱዳን ውስጥ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ጸረ-መፈንቅለ መንግስት ተቃውሞ አንድ ሰው ተገደለ

ሱዳን ውስጥ ተቃውሞ ሰልፈኞች በደህንነት ኃይሎች ላይ መልሰው የአስለቃሽ ጭስ ቋቶችን ወርውረዋል። ግንቦት 19/2022 የተነሳ

የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ፖለቲካዊ ሽግግርን በማደናቀፍ ስልጣን የያዘውን የጦር ኃይል ለመቃወም እንደ አዲስ ወደ አደባባይ ከወጡት ሰልፈኞች መካከል አንዱን መግደላቸውን የህክምና ባለሙያዎች አስታወቁ።

እስካሁን ማንነቱ ይፋ ያልተደረገው ግለሰብ ፣ ደረቱ ላይ በጥይት በመመታቱ ፣ የመናገሻዎ ከተማ መንትያ ተብለ በምትጠራው ኡምዱርማን ከተማ ውስጥ ህይወቱ እንዳለፈ ፣ የሱዳን ሃኪሞች የአፍቃሪ-ዴሞክራሲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

በጎረጎሳዊያኑ ጥቅምት 25 በሱዳኑ የጦር መሪ አብደል ፈታ አል ቡርሃን የተመራው መፈንቅለ -መንግስት ከተከናወነ ወዲህ ፣ በተከታታሉ ጸረ-መፈንቅለ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች የሞቱ ሰወች ቁጥር ከአሁኑ ጋር ተዳምሮ 96 መድረሱን ኮሚቴው ገልጿል።

የቅዳሜ ዕለቱ ተቃውሞ፣ ሀሙስ ዕለት በዋነኝነት በካርቱም ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የተሳተፉበትን የስልጣን ንጥቂያን ለመቃወም እና የሲቪሎች አስተዳዳር እንዲመሰረት ዳግም ለመጠየቅ የተደረገውን ሰልፍ የተከተለ ነው።

በሀሙሱ የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት 100 ያህል ሰዎች መጎዳታቸውን የሀኪሞች ኮሚቴ አስታውቋል።በተመሳሳይ የሱዳን ኮሚኒስት ፓርቲ አባል የሆኑ ሁለት ጸረ-መፈንቅለ መንግስት መሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኃላ በቀጣዩ ቀን ተለቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከቀጠናዊው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን ጋር በመሆን ፣ ከዓለም ድሃ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት ፣ የሀገሪቱ ህዝቦች የሚመሩት ንግግር እንዲደረግ ግፊት ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ዘገባው የኤ ኤፍፒ ነው።