"የዩክሬን አጎራባች የሞልዶቫ ሉዓላዊነት ጥቃት ሊደርስበት አይገባም" የተመድ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እና የሞልዶቫ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊያ ጋቫርሊታ ሞልዶቫ እአአ ግንቦት 9/2022

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ የምታካሂደው ጦርነት ሊስፋፋ የመቻሉ አደጋ እንደሚያሳስባቸው ትናንት ሞልዶቫን የጎበኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ገለጹ።

ጉቴሬዥ ከሞልዶቫ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊያ ጋቫርሊታ ጋር ባካሄዱት ጋዜጣዊ ጉባዔ ሩሲያ ዩክሬን ላይ የምታካሂደው ጦርነት መቀጠሉ እና ሊስፋፋም የሚችል መሆኑ ብሎም በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በዐለም በጠቅላላ እያስከተለ ያለው አንድምታ በጥልቅ ያሳስበኛል ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነቷ ሞልዶቫን በክሬምሊን በምትደገፈው ተገንጣይዋ ትራንሲስትሪያ ክፍለ ግዛት በኩል ሁለተኛዋ የውጊያ ግንባር ልታደርጋት ትችላለች የሚል ዓለም አቀፍ ሥጋት አለ። ጉቴሬዥ "ሉዓላዊነታችሁ፣ ነጻነታችሁ እና ባለፉት ሦስት አሰርት ያስመዘገባችሁት እርምጃ ጥቃት ሊቃጣበት አይገባም" ብለዋል።

የሩሲያ የዩክሬን ወረራ መቆም አለበት ያሉት ጉቴሬዥ ሁለቱ ወገኖች በዓለም አቀፍ ህግ እና በተመድ ቻርተር መሰረት በአስቸኳይ በድርድር መፍትሄ ለማምጣት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንዲያጠናክሩ እማጸናለሁ ብለዋል።